Widgetized Section

Go to Admin » Appearance » Widgets » and move Gabfire Widget: Social into that MastheadOverlay zone

የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር ፕሬዚዳንት ፖል ካጋሜ በራሳቸውና በአፍሪካ መሪዎች ስም ለዶ/ር አብይ የደስታ መግለጫ ላኩ


አዲስ አበባ፣ መጋቢት 20፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የወቅቱ የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበርና የሩዋንዳ ፕሬዚዳንት ፖል ካጋሜ በራሳቸውና በአፍሪካ ሀገራት መሪዎች ስም ለዶከተር አብይ አህመድ የደስታ መግለጫ አስተላልፈዋል።

ፕሬዚዳንት ፖል ካጋሜ በይፋዊ የትዊተር ገፃቸው ላይ ባሰፈሩት መልእክት፥ የኢህአዴግ ሊቀመንበር በመሆን ለተመረጡት ለዶክተር አብይ አህመድ ስልክ በመደወል ደስታቸውን መግለፃቸውን አስታውቀዋል።

ቀጣዩ መሪውን ለመረጠው የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር እና ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብም የእንኳን ደስ ያላችሁ መልእክታቸውን በዶክተር አብይ በኩል ማስተላለፋቸውንም አስታውቀዋል።

ፕሬዚዳንት ፖል ካጋሜ ባስተላለፉት መልእከት፥ “እንደ አፍሪካ ህብረት ሊቀመንበርነቴ እና በሌሎች የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች ስም ከኢትዮጵያ ህዝብ እና መንግስት ጎን እንደምንቆም እንገልፃለን” ብለዋል።

ኢትዮጵያም በአህጉሪቱ ያላትን ታሪካዊ የወሳኝነት ሚናዋን አጠናክራ እንደምትቀጥል ሙሉ እምነት አለኝ ሲሉም ፕሬዚዳንት ፖል ካጋሜ ገልፀዋል።

የኢህአዴግ ምክር ቤት ባሳለፍነው ማክሰኞ ዶክተር አብይ አህመድን የግንባሩ ሊቀመንበር አድርጎ መምረጡ ይታወሳል።

የኢህአዴግ ፅህፈት ቤት ትናንት በሰጠው መግለጫም፥ የድርጅቱ ሊቀ መንበር በመሆን የተመረጡት ዶክተር አብይ አህመድ በአሰራሩ መሰረት ጠቅላይ ሚኒስትር እደሚሆኑ አስታውቋል።

በዚህም መሰረት ዶክተር አብይ አህመድ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው የሚሰየሙ ይሆናል ብሏል ፅህፈት ቤቱ በመግለጫው።

የኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፊታችን ቅዳሜ በሚያካሂደው ልዩ ስብሰባ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትርን ይሰይማል ተብሎ ይጠበቃል።