Widgetized Section

Go to Admin » Appearance » Widgets » and move Gabfire Widget: Social into that MastheadOverlay zone

ፋና ቴሌቪዥን ተመረቀ


አዲስ አበባ፣ ጥር 26፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ፋና ቴሌቪዥን ተመረቀ።

የቴለቪዥን ጣቢያውንም የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ መርቀውታል።

የፋና ቴሌቪዥን ምረቃትን አስመልክቶ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ወልዱ ይመስል፥ የቴሌቪዥን ጣቢያውን እዚህ እንዲደርስ ረዥም ጊዜ መውሰዱን እና ሰፊ መሰራቱን ነው የተናገሩት።

የቴሌቪዥን ጣቢያው ተመርቆ ዛሬ መደበኛ ስርጭት መጀመሩም የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ሀገራዊ እና ተቋማዊ ሀላፊነት ከፍ እንደሚያደርገው አስታውቀዋል።

ፋና ባለፉት 23 ዓመታት በሬዲዮ ዘርፍ ሰፊ ስራ የሰራ ቢሆንም የሚቀሩት ስራዎች ግን ይበዛሉ ያሉት ዋና ስራ አስፈፃሚው፥ በዚህ ላይ ቴሌቪዥን ሲጨመር ሀላፊነቱ ከፍ እንደሚል በማንሳት ተቋሙ በዛሬው ምረቃ ለዚህ ሀላፊነት ዝግጁ መሆኑን እንደሚያረጋግጥ አመልክተዋል።

ሀገረን ከመለወጥ እና የህዝቡን ኑሮ ከማሻሻል አንፃር ፋና በሬዲዮው መስክ በተነፃፃሪ ጥሩ ስራ ሰርቷል ያሉት አቶ ወልዱ፥ ይህንንም ያደረገው ህዝቡን በማሳተፍ ዜጎች ሃሳባቸውን የሚያቀርቡበት መድረክ በመሆን ነው ብለዋል።

ወደ ቴሌቪዥን ዘርፍም ሲመጣ ተቋሙ ከቀረፃ እስከ ስርጭት ድረስ ዓለም የደረሰበትን የዲጂታል ቴክኖሎጂን በመጠቀም በሀገሪቱ የመጀመሪያውን ሙሉ የኤች ዲ የቴሌቪዥን ስርጭት ይዞ መምጣቱን አስታውቀዋል።

ከይዘት አንፃርም በዓለም አቀፍ ደረጃ ሰፊ ጥናት በማድረግ የተለያዩ ፎርማቶች እንደተቀረፁ እና ከጊዜ ሂደት የህብረተሰቡን ፍላጎት እና የሚለወጥን ዓለም እየተከተለ የሚቀየር የፎርማት አቀራረፅ መከተሉን ገልፀዋል።

ፎርማቶቹ እስካሁን ያልተለመዱ፤ በከተሞች ምሁሩ በአጠቃላይ ህዝቡ ለሀገር እድገት ሀሳቡን እንዲያዋጣ የሚያስችሉ መሆናቸውንም አንስተዋል።

በአጠቃላይ በቴሌቪዥን ኢንዱስትሪ ውስጥ ተወዳዳሪ እና የተሻለ ሆኖ ለመገኘት እና አትራፊ ሆኖ ለመቀጠል የሚያስችለው ሁለገብ እና ተለዋዋጭ የሆነ የይዘት ዝግጅት ማድረጉን ገልፀው፥ እስካሁን በነበረው የስርጭት ቆይታም ያገኘው ግብረ መልስ ይህንን የሚያረጋግጥ ነው ብለዋል።

የዜጎችን ፈጣን የመረጃ እና የህይወት ለውጥ ፍላጎትን መሰረት በማድረግም ለዜጎች ፍጥነት ለመራመድ እና ከዚሁ ጋር አብሮ ለሀገር ለውጥ በመስራት የተሻለ ሀይወት እንፈጥራለን በሚልም “በህይወት ፍጥነት” የሚል መሪ ቃልንም ይዞ ፋና ቴሌቪዥን መምጣቱንም አቶ ወልዱ ተናግረዋል።