Widgetized Section

Go to Admin » Appearance » Widgets » and move Gabfire Widget: Social into that MastheadOverlay zone

የኦህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ የተለያዩ ውሳኔዎችን በማሳለፍ ስብሰባውን አጠናቀቀ


አዲስ አበባ፣ ጥር 29፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) ለ10 ቀናት በአዳማ ስብሰባውን ሲያካሂድ የቆየው የኦሮሞ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት/ኦህዴድ/ ማዕከላዊ ኮሚቴ የተለያዩ ውሳኔዎችን በማሳለፍ ስብሰባውን አጠናቋል።

ማዕከላዊ ኮሚቴው በቆይታው ውስጠ ዴሞክራሲን ለማጎልበት፣ አንድነትን ለማጠናከር እና የአመራር ስብዕናን ለማጠናከር በጥልቀት ሲወያይ መቆየቱን ባወጣው መግለጫ ጠቁሟል።

የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ባስቀመጠው የተሃድሶ መስመር መሰረት በኢኮኖሚ፣ ፖለቲካ እና ማህበራዊ ዘርፎች ጥልቅ ግምገማ ሲያደርግ መቆየቱን ነው ያስታወቀው።

በተለይም የሀገሪቱን ብሎም የክልሉን ሰላም ለማስጠበቅ እና ልማትን ለማስቀጠል በጥልቀት ሲወያይ የነበረው ማዕከላዊ ኮሚቴው ድርጅቱ የህዝቡን ቅሬታ በማድመጥ አቅጣጫዎችን በማመላከት ወደፊት የተሻለ ስራ ለመስራት ዝግጅት ማድረጉን ጠቁሟል።

ዴሞክራሲያዊ እና ህዝባዊ ወገንተኝነት ባህሉንም በማጠናከር ህብረተሰቡ የሚያነሳቸውን ቅሬታዎች በማድመጥ ከልብ ይቅርታ መጠየቅ እና የእርምት እርምጃዎችን መውሰድ አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱንም ማዕከላዊ ኮሚቴው መወያየቱን ነው በመግለጫው ላይ የገለፀው።

የፌደራል ስርዓቱን አደጋ ላይ የሚጥሉ ችግሮችን ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ በመለየት የህብረተሰቡን ፍላጎት ለማሟላት አፋጣኝ መፍትሄ መስጠት ወሳኝ መሆኑንም አስምሮበታል።

ፍትሃዊ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን እና የፖለቲካ ተሳትፎን ለማረጋገጥ የኦሮሞን ህዝብ በሰፊው ማሳተፍ ጊዜ የማይሰጠው ጉዳይ መሆኑንም ተመልክቷል።

የኦሮሞ ህዝብ ከሌሎች የሀገሪቱ ብሄሮች እና ብሄረሰቦች ጋር በሰላም በመኖር ያካበተውን ልምድ በመጠቀም የሀገር ግንባታ ልክ እንደትናንቱ ማጠናከር አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱንም ማዕከላዊ ኮሚቴው ተቀብሏል።

ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ ከኢህአዴግ እህት ድርጅቶች ጋር ያለው ግንኙነት እንዲጠናከር ኦህዴድ እንደሚሰራም አረጋግጧል።

ኪራይ ሰብሳቢነትን እና የመልካም አስተዳደር ችግር የፌደራል ስርዓቱን አደጋ ላይ የሚጥል ነው ያለው ኮሚቴው፥ ችግሮችን በጊዜ በመፍታት የህብረተሰቡን እርካታ መጠበቅ እንደሚያስፈልግ ነው ያመለከተው።

ለወጣቱ በስፋት የስራ እድል በመፍጠር የሰላማዊ ትግል እና የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ አካል እንዲሆን፣ በጥሞና በማድመጥ እና በመደገፍ የነገ የሀገሪቱ ተረካቢ እንዲሆን በተሻለ ይሰራልም ብሏል።

ክልሉ ከኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ጋር በሚዋሰንባቸው አካባቢዎች ተከስቶ በነበረው ግጭት ሳቢያ ተፈናቅለው የነበሩ ዜጎችን ለመደገፍ እና ለማቋቋም የተጀመረው ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቋል።

ማእከላዊ ኮሚቴው በኢህአዴግ ምክር ቤት 14 አባላቱን ተጠያቂነትን ለማስፈን እና የተሻለ ትግልን ለማካሄድ በአዳዲስ ጠንካራ አመራሮች መተካቱንም አስታውቋል።

አራት የማዕከላዊ ኮሚቴው አባላት እስከ ቀጣዩ ድርጅታዊ ጉባኤ ድረስ ታግደው እንዲቆዩ ውሳኔ ያሳለፈ ሲሆን፥ አንድ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባልንም በማስጠንቀቂያ እንዲታለፉ መወሰኑን አስታውቋል።

የኦሮሚኛ ቋንቋን የፌደራል ቋንቋ ለማድረግ፣ ኦሮሚያ ከአዲስ አበባ የምታገኘውን ህገመንግስታዊ ልዩ ጥቅም እንዲፈፀም፣ የልዩ ዞን እና የአዲስ አበባ ወሰንን በዘለቄታው ለማካለል ኦህዴድ ተግቶ እንደሚሰራም ማዕከላዊ ኮሚቴው አስታውቋል።