Widgetized Section

Go to Admin » Appearance » Widgets » and move Gabfire Widget: Social into that MastheadOverlay zone

ክልሎች የወጣቶች ተዘዋዋሪ ፈንድን በአግባቡ እየተጠቀሙ አይደለም


አዲስ አበባ ፣ የካቲት 2 ፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ወጣቶችን በልዩ ሁኔታ ተጠቃሚ ያደርጋል ተብሎ በመንግስት የተበጀተውን ተዘዋዋሪ ፈንድ ክልሎች በአግባቡ እየተጠቀሙ አለመሆኑን የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር ገልጿል።

ወጣቶችን ተጠቃሚ ያደርጋል ተብሎ የታቀደው የወጣቶች ተዘዋዋሪ ፈንድ ከተበጀተ ሁለት ዓመት ሊሞላው ጥቂት ጊዜያት ብቻ ቀርተውታል።

ይኼው 10 ቢሊየን ብር የወጣቶች ተዘዋዋሪ ፈንድ በመላ ሀገሪቱ የሚገኙ ወጣቶች በመንግስት አዋጭነታቸው በተረጋገጠባቸው የስራ መስኮች ተደራጅተው ተጠቃሚ እንዲሆኑ ታሳቢ ያደረገ ነው።

ይሁን እንጂ ክልሎች በፍጥነት ተደራሽ ባለማድረጋቸው ምክንያት፥ ተዘዋዋሪ ፈንዱን በአግባቡ መጠቀም እንዳልቻሉ ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ያነጋገራቸው ወጣቶች ይናገራሉ።

አዲስ አበባን ጨምሮ አማራ፣ ትግራይ፣ አፋር፣ ጋምቤላና የሀረሪ ክልል ፈንዱን በአግባቡ እንዳልተጠቀሙበት፥ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የበጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ከገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር ጋር ባደረገው ውይይት አንስቷል።

ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አንዱ የሆነው የአማራ ክልል የመጀመሪያ ዙር የተዘዋዋሪ ፈንዱን ያልወሰደ ሲሆን፥ አሁን ላይ ከፌደራል መንግስት 1 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር በማስለቀቅ እስካሁን 892 ሚሊየን ብር ለስራ አጥ ወጣቶች አሰራጭቷል።

ገንዘቡ በተለያዩ ዘርፎች ለተሰማሩ 20 ሺህ 734 እና በኢንተርፕራይዝ ደረጃ ለተደራጁ 3 ሺህ 728 ወጣቶች የተከፋፈለ ነው፤ ወጣቶችም በማምረቻ፣ በግንባታ፣ በግብርናና በንግድ እንዲሁም በሀገልግሎት ተደራጅተው እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ።

የደቡብ ክልል በበኩሉ ለክልሉ ከተፈቀደው የተዘዋዋሪ ፈንድ እስካሁን ከገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር ያልተረከበው 480 ሚሊየን ብር ያህል ነው።

የደቡብ ክልል የገጠር ስራ እድል ፈጠራ ኤጀንሲ ስራ አስኪያጅ አቶ ኢዘዲን ሙስባህ እንዳሉት፥ በገጠር ከ62 ሺህ በላይ ወጣቶች በከብት ማድለብ፣ በመስኖ ልማትና የወተት ተዋጽኦዎችን በማቅረብ ተደራጅተዋል።

ከ25 ሺህ በላይ የሚሆኑት ደግሞ በከተማ በተለያዩ የስራ ዘርፎች መደራጀታቸውን ተናግረዋል።

የፈንዱ ባለቤት የሆኑ ስራ አጥ ወጣቶችን መለየቱ ጊዜ በመውሰዱ ምክንያት ፈንዱን ከመጠቀም አንጻር መዘግየት መታየቱንም ነው የተናገሩት፤ ተጠቃሚ ከሆኑ ወጣቶች መካከል ብድር መመለስ የጀመሩ እንዳሉ በመጥቀስ።

እስካሁንም 25 ሚሊየን ያህል ገንዘብ ወጣቶች ከተበደሩት ገንዘብ ላይ ተመላሽ አድርገዋል ነው የተባለው፤ ይሁን እንጂ የተዘዋዋሪ ፈንዱ አፈጻጸም በሁሉም ክልሎች ወጥ በሆነ መንገድ እየተተገበረ አይደለም።

ለዚህ ደግሞ በጀቱ ከፌደራል መንግስት ቢለቀቅም ባለፉት ስድስት ወራት ክልሎች ጥያቄ አለማቀረባቸውን፥ የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስትሩ ዶክተር አብርሀም ተከስተ ገልጸዋል።

እስካሁንም ከተመደበው 10 ቢሊየን የወጣቶች ተዘዋዋሪ ፈንድ ውስጥ ለክልሎች የተሰራጨው 4 ቢሊየን የሚሆነው ብቻ እንደሆነም ዶክተር አብርሃም ይገልጻሉ።

በበጀት ዓመቱ ቀሪ ጊዜያትም ክልሎች በጀቱን ወስደው ወጣቱን ተጠቃሚ እንዲያደርጉ ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል ሚኒስትሩ።

Leave a Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.