Widgetized Section

Go to Admin » Appearance » Widgets » and move Gabfire Widget: Social into that MastheadOverlay zone

ፌዴራል ፖሊስ ‹‹ቄሮ›› ተብሎ በሚጠራው ቡድን ላይ ጥልቅ ምርመራ መጀመሩ ተሰማ


የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ‹‹ቄሮ›› ተብሎ በሚጠራው የኦሮሞ ወጣቶች ቡድን እንቅስቃሴ ላይ ጥልቅ ምርመራ መጀመሩን ሪፖርተር ያገኛቸው መረጃዎች አመለከቱ፡፡

‹‹ቄሮ›› በሚል ስያሜ የሚታወቅ የኦሮሞ ወጣቶች ህቡዕ እንቅስቃሴ በምሥራቅ ሐረርጌ መንሰራፋቱን፣ በአካባቢው የመንግሥት መዋቅርን ተልዕኮ የመንጠቅ አዝማሚያ የያዘ እንቅስቃሴ ማከናወን ከጀመረ ወራት መቆጠራቸውን ምንጮች ገልጸዋል፡፡

አዲስ አበባን ከጂቡቲ ወደብ የሚያገናኘው ዋና መንገድ በአፋር ክልል አንዳንድ አካባቢዎች በመበላሸቱ ሾፌሮች ከአዋሽ በድሬዳዋ አድርገው ወደ ጂቡቲ የሚያደርጉት ጉዞ በዚህ የወጣቶች ቡድን አልፎ አልፎ እየተስተጓጎለ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ መንገዶችን በመዝጋት የከባድ ተሽከርካሪዎችን ጉዞ የማሰናከል፣ እንዲሁም ጭነቶችን በማራገፍ ለአካባቢው ኅብረተሰብ የማከፋፈል ተግባሮች መፈጸማቸውን፣ የአካባቢውን የመንግሥት መዋቅር የማዘዝና ትዕዛዙን በማይፈጽሙ አመራሮች ላይ ዕርምጃ የመውሰድ ድርጊቶች መፈጸማቸውንም ምንጮች ጠቁመዋል፡፡ በኅዳር ወር መጨረሻ አካባቢ ጋራ ሙለታ በሚባል አካባቢ ከሚገኝ እስር ቤት እስረኞችን የማስለቀቅ ድርጊት መፈጸሙንም ምንጮች አስታውቀዋል፡፡

የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን በአሁኑ ወቅት በዚህ የወጣቶች ቡድን ላይ ምርመራ መጀመሩን፣ ይህንን ምርመራ የሚያከናውን ግብረ ኃይልም መቀመጫውን በድሬዳዋ ከተማ አድርጎ መሰማራቱን ለማወቅ ተችሏል፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች ግጭት ዜጎች እንዴት ሊፈናቀሉ እንደቻሉ ምርመራ እንዲያደርግ ያሰማራው ሱፐርቪዥን ቡድን ያጠናቀረውን ሪፖርት፣ ሐሙስ ታኅሳስ 26 ቀን 2010 ዓ.ም. ለምክር ቤቱ ባቀረበበት ወቅት የተገኙት የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ አሰፋ በዩም ይህንኑ አረጋግጠዋል፡፡

ራሱን ‹‹ቄሮ›› ብሎ የሚጠራው የወጣቶች እንቅስቃሴ በምሥራቅ ሐረርጌ ሥጋት የፈጠረ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡ የመከላከያና የፌዴራል ፖሊስ አባላትን ተልዕኮ የማስተጓጎልና አንዳንዴም ግብግብ ውስጥ ሲገባ እንደሚታይ ገልጸዋል፡፡

በዚህ የወጣቶች እንቀስቃሴ ውስጥ የአካባቢ ሚሊሻዎች፣ አንዳንድ የአካባቢው ፖሊሶችና የወረዳ አመራሮች ተሳትፎ ስለማድረጋቸው የጠቆሙት ኮሚሽነሩ፣ የመንግሥት ተሽከርካሪዎችም ጥቅም ላይ ውለው እንደታዩ አብራርተዋል፡፡ ይህ ኃይል እንዴት ተደራጀ? ዓላማው ምንድነው? የሚለውን የተጀመረው ምርመራ በጥልቀት ዘልቆ የሚመልሰው ጥያቄ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ጉዳዩን በተመለከተ የኦሮሚያ ክልል ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊን ለማነጋገር የተደረገው ጥረት አልተሳካም፡፡ጠናቀረውግምን- T2
Source: Reporter