Widgetized Section

Go to Admin » Appearance » Widgets » and move Gabfire Widget: Social into that MastheadOverlay zone

አገር በመክዳትና በሽብር ወንጀል ውስጥ ተሳትፈዋል የተባሉ የመከላከያ ሠራዊት አባላት ተከሰሱ

ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ለመጠበቅ የተጣለባቸውን አደራ በመተው፣ የኦነግን የሽብር ተልዕኮ ለመፈጸም አባል ሆነውና ሌሎችንም ሲመለምሉ ነበር የተባሉ አምስት የመከላከያ ሠራዊት ባልደረቦች፣ የሽብር ተግባር ወንጀል በመፈጸም ተጠርጥረው ክስ ተመሠረተባቸው፡፡

ተከሳሾቹ የደቡብ ምዕራብ ዕዝ አባላት መሆናቸውንና በሶማሌ ክልል ልዩ ስሙ ካሉብ ነዳጅ ማውጫ አካባቢ ተመድበው ይሠሩ እንደነበር፣ የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የመሠረተባቸው ክስ ያስረዳል፡፡

በሽብር ተግባር ወንጀል የተከሰሱት ወታደር ኢብራሂም ጉሬ፣ ምክትል አሥር አለቃ እስክንድር አደም፣ አሥር አለቃ ሽመልስ ብርሃኑ፣ ወታደር ጫላ ኢሳና ወታደር ሀብታሙ ፋና መሆናቸውን፣ ሁሉም ተከሳሾች የሱማሌ ክልል ቆራኔ ደብወይኒ ነዋሪዎች መሆናቸው በክሱ ተጠቁሟል፡፡

ተከሳሾቹ ተመድበው ይሠሩበት የነበረውን ወታደራዊ ተግባር በአግባቡ መፈጸም ሲገባቸው፣ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) ዓላማ ለማስፈጸም፣ የሠራዊቱን አባላትና ሌሎችን በአባልነት ይመለምሉ እንደነበር ዓቃቤ ሕግ በክሱ አስረድቷል፡፡ በሶማሌ ክልል ልዩ ስሙ ካሉብ ነዳጅ ማውጫ ተብሎ በሚጠራው ሥፍራ፣ በግዳጅ ላይ የነበሩ የጦር ሠራዊት አባላትን ይመለምሉ እንደነበርም ተገልጿል፡፡

‹‹ኦነግን እንቀላቀል›› በማለት የታጠቁትን የጦር መሣሪያ እንደያዙ በቅስቀሳና ምልመላ ላይ መሳተፋቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ ገልጿል፡፡ ተከሳሾቹ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32(1ሀ)፣ 38 እና የፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ 7(1) ሥር የተደነገገውን ተላልፈው መገኘታቸው፣ በፈጸሙት የሽብርተኛ ድርጅት ውስጥ መሳተፍ ወንጀል ክስ ቀርቦባቸዋል፡፡
ምንጭ: ሪፓርተር