Widgetized Section

Go to Admin » Appearance » Widgets » and move Gabfire Widget: Social into that MastheadOverlay zone

መንገደኞች ለግል መገልገያ ብቻ የሚጠቀሙባቸውን እቃዎች ወደ ሃገር ውስጥ ከታክስ ነጻ እንዲያስገቡ የሚፈቅድ መመሪያ ይፋ ሆነ


አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 24፣ 2010 (ኤፍ. ቢ. ሲ.) መንገደኞች ለግል መገልገያ ብቻ የሚጠቀሙባቸውን እቃዎች ወደ ሃገር ውስጥ ከታክስ ነጻ እንዲያስገቡ የሚፈቅድ መመሪያ ይፋ ሆነ።

ለንግድ የማይዉሉ ወደ አገር ዉስጥ የሚገቡ የግል መገልገያ እቃዎችን ከቀረጥና ታክስ ነጻ ሆነው እንዲገቡ የወጣውን መመሪያ የገንዘብ እና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር፤ በጉምሩክ አዋጁ ተፈጻሚ ይሆን ዘንድ መላካቸውን በሚኒስትር መስሪያ ቤቱ የህግ አገልግሎት ዳይሬክሩ አቶ ቦቹ ስንታየሁ ገልጸዋል።

መመሪያው በአየርም ሆነ በየብስ ከውጭ አገር የሚመጡ መንገደኞች፣ ተመላሽ ኢትዮጵያውያንና በተለያዩ አጋጣሚዎች የሚመጡ የውጭ አገር ዜጎችም በመመሪያው ተጠቃሚ ይሆናሉ ነው የተባለው።

መመሪያው ከታህሳስ 6 ቀን 2010 ዓመተ ምህረት ጀምሮ የፀና መሆኑ የተገለፀ ሲሆን፥ መንገደኞችም የኤሌክትሮኒክስ፣ የጽህፈት ህትመት እና ኮፒ አገልግሎት እቃዎችን፣ የሙዚቃ ማጫወቻ እና ተዛማጅ መሳሪያዎች፣ ለቤት ውስጥ አገልግሎት የሚዉሉ የማብሰያ እና መሰል እቃዎችን በነጻ እንዲገቡ ፈቅዷል።

በተጨማሪም ሌሎችም በ26 አይነት የተመደቡ 351 መገልገያ የእቃ አይነቶች ላይ የሚገቡበትን ብዛትና መጠን መመሪያው አካቷል።

ለምግብነት የሚያገለግሉ እቃዎች እስከ 20 ኪሎ በጉዟቸው ወቅት እንዲያስገቡና እንዲያስወጡ ሲፈቀድ፥ ሁለት ሞባይል ቀፎዎችና ኤክስተርናል ሃርድዲስክ እንደዚሁም ቴሌቪዥን ከነስታንዱ፣ መገልገያ ካሜራ፣ ላፕቶፕ ኮምፒተር አንዳንድ ይዞ እንዲሁም፥ አምስት ፍላሽ ዲስኮች ማስገባት እንደሚቻልም በመመሪያው ተካቷል።

በመመሪያው ያልተካተቱ ሌሎች እቃዎች ሲመጡም በልዩ ሁኔታ በባለስለጣኑ ዉሳኔ እንደሚሰጥባቸው ነው የተነገረው።

በዚህም ወጥ በሆነ የታሪፍ ምጣኔ የማይስተናገዱ እቃዎችም ባለመብቱ ሊገለገልበት ከሚችለው መጠን በላይ በተደጋጋሚ ሲያስገባ፣ ለንግድ የሚዉሉ መገለገያ እቃዎችን ሲያስገባና ለንግድ የማይዉሉ ተብለው ከተቀመጠው መመሪያ ዉጭ የሆኑ ዕቃዎችን የሚያስገባ ከሆነ ዕገዳ ይጣልበታል።

ዳይሬክተሩ ለመገልገያ ተብለው የሚገቡ እቃዎችን ለንግድ ስራ ማዋል እንደማይቻል ገልጸዋል።