Widgetized Section

Go to Admin » Appearance » Widgets » and move Gabfire Widget: Social into that MastheadOverlay zone

አቶ ዘላለም ጀማነህ በስድስት ዓመት እስራት ተቀጡ


አዲስ አበባ፣ ህዳር 28፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በሙስና ወንጀል ተከሰው የነበሩት በምክትል ፕሬዚዳንት ማዕረግ የኦሮሚያ ክልል ግብርና ቢሮ የቀድሞ ኃላፊ አቶ ዘላለም ጀማነህ በእስራት እና በገንዘብ ተቀጡ።

አቶ ዘላለም የማይታወቅ ሃብት ማከበት እና በክልሉ መንግስትና ድርጅት ውስጥ ከፍተኛ አመራር በነበሩበት ወቅት የተጣለባቸውን ሕዝባዊ አደራና ወገንተኝነት ወደ ጎን በመተው በክልሉ በተለያዩ የስልጣን ደረጃ በሰሩባቸው ጊዜያት ለዘመዶቻቸው በርካታ መሬት እንዲወስዱ በማድረግ ሙስና ወንጀል 14 ክሶች ተመስርቶባቸው እንደነበር ይታወሳል።

ጉዳያቸውን ሲመለከት የቆየው የፊንፊኔ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዛሬ በዋለው ችሎት አቶ ዘላለም በስድስት ዓመት ፅኑ እስራት እና በ11 ሺህ ብር እንዲቀጡ ውሳኔ አሳልፏል።

በእርሳቸው ስም የተመዘገበ የጭነት ተሽከርካሪ እንዲወረስም ነው ያዘዘው።

በክስ መዝገቡ ስር ሁለተኛ ተከሳሽ የሆኑት እና የሙስና ወንጀሉን ተባብሮ በመፈፀም የተከሰሱት የአቶ ዘላለም ጀማነህ ባለቤት ወይዘሮ ምስራቅ ቂጣታ በአምስት ዓመት ከስድስት ወር እስራት እና በ11 ሺህ ብር እንዲቀጡ ወስኗል።

በተከሳሿ ስም በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና በአዋሽ ባንክ የተቀመጠ ገንዘብም እንዲወረስ አዟል።

ፍርድ ቤቱ የ11 ሺህ ብር ቅጣቱ ተከፍሎ የአምስት ዓመት እስራት ሳይፈፀም በሁለት ዓመት ገደብ እንዲታይ ውሳኔ አሳልፏል።

ሶስተኛ ተከሳሽ ሚርጌሴ ገመዳ በአምስት ዓመት ከስድስት ወር እስራት እና 11 ሺህ ብር እንዲቀጡ ነው ፍርድ ቤቱ የወሰነው።