Widgetized Section

Go to Admin » Appearance » Widgets » and move Gabfire Widget: Social into that MastheadOverlay zone

የአማራ የትግራይና የደቡብ ክልሎች በግጭቱ ለተፈናቀሉ ወገኖች የ30 ሚሊየን ብር ድጋፍ አደረጉ


አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 23፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) የአማራ የትግራይና የደቡብ ክልሎች በኦሮሚያና ኢትዮጵያ ሶማሌ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች ተፈጥሮ በነበረው ግጭት ለተፈናቀሉ ወገኖች መልሶ ማቋቋሚያ የ30 ሚሊየን ብር ድጋፍ አደረጉ።

የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ሚኒስትር ዲኤታ ፍሬህይወት አያሌው፥ ክልሎቹ እያንዳንዳቸው 10 ሚሊየን ብር ድጋፍ ማድረጋቸውን ገልፀዋል።

የገንዘብ ድጋፉ በብሔራዊ አደጋና ስራ አመራር ኮሚሽን አማካኝነት ለተጎጂዎች እንደሚደርስም አረጋግጠዋል።

በአሁኑ ወቅት ከተለያዩ አካባቢዎች ለተፈናቃዮች መቋቋሚያ ድጋፍ እየተደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል።

በተለያየ መልኩ የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመቋቋምና ለማቃለል ክልሎች እርስ በእርስ የሚያደርጉት መደጋገፍ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ነው ሚኒስትር ዲኤታዋ ያመላከቱት።

ወይዘሮ ፍሬህይወት ሁሉም የሀገሪቱ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በግጭቱ የተፈናቀሉ ወገኖችን ለማቋቋም እያከናወኑ ያሉትን ተግባርም አድንቀዋል።

መንግስት የተፈናቀሉ ዜጎች ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ ከሀገር ሽማግሌዎች፣ ሃይማኖት አባቶችና የጎሳ መሪዎች ጋር እያከናወነ ያለውን ተግባር አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተናግረዋል።

ችግሮችን ለመፍታት በሚያስችል መልኩ መንግስት የሰላም ጉባዔዎችን እንደሚያካሄድ ጠቁመው፥ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ለሰላም መስፈንና የተጀመረውን ልማት በተጠናከረ መልኩ ለማስቀጠል ርብርብ እንዲያደርግ ነው ጥሪ ያቀረቡት።

ሚኒስትር ዲኤታዋ ኢትዮጵያውያን እንደቀደመው ሁሉ ለአካባቢ ሰላም ዘብ መቆም እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

ምንጭ፦ኢዜአ