Widgetized Section

Go to Admin » Appearance » Widgets » and move Gabfire Widget: Social into that MastheadOverlay zone

‹‹አቶ አባዱላ በቴሌቪዥን ወጥተው መናገራቸው ስህተት ነው››


የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አባዱላ ገመዳ ከአፈ ጉባዔነት ለመልቀቅ ጥያቄ ስለማቅረባቸው በቴሌቪዥን ወጥተው መናገራቸው ስህተት መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ገለጹ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ዛሬ ጥቅምት 30 ቀን 2010 ዓ.ም. ከቀትር በኋላ በጽሕፈት ቤታቸው በሰጡት መግለጫ፣ ከሪፖርተር በኢሕአዴግ ውስጥ ስላለ ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት ጥያቄ ቀርቦላቸዋል ነው ይኼን ምላሽ የሰጡት፡፡

‹‹ኢሕአዴግ የሚታወቅበት ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት በአሁኑ ወቅት አለ ማለት ይቻላል ወይ? አፈ ጉባዔ አባዱላ የኦሮሞ ሕዝብን መብት ለማስከበር እታገላለው ማለታቸው የዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት በኢሕአዴግ ውስጥ መጥፋቱን እንደሚያመላክትና ይህም ኢሕአዴግን ሊበትነው አይችልም ወይ?›› በሚል ከሪፖርተር ለቀረበላቸው ጥያቄ፣ ‹‹ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት የማይገረሰስ የኢሕአዴግ መርህ ነው፤›› ሲሉ መልሰዋል፡፡

“አፈ ጉባዔ አባዱላ መልቀቂያ ስለማቅረባቸው ሪፖርተር በመዘገቡና ከወጣ አይቀር ሐሳቤን በደንብ መግለጽ አለብኝ በማለት ወደ ሚዲያ ሊሄዱ ችለዋል። ወደ ሚዲያ መሄዳቸው ስህተት ነው። ምክንያቱም በውስጣችን እንፈታው ነበር። ሆኖም አሁንም በድርድር ላይ የለ ጉዳይ በመሆኑ ዲሞክራሲያዊ ማእከላዊነትን ጥሰዋል ማለት አይቻልም፤” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።

ነገር ግን ወደ ሚዲያ መውጣታቸው ስህተት ነበር ብለዋል፡፡ በእንደዚህ ዓይነት ጉዳይ ኢሕአዴግን የሚፈርስ አድርጎ ማሰብ ድርጅቱን አለማወቅ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም፣ ‹‹ታላቁ መሪያችን አቶ መለስ ዜናዊ በሞቱ ጊዜ እንኳን አልተበተነም፤›› ብለዋል፡፡

አቶ አባዱላ ከአፈ ጉባዔነታቸው የሥራ መልቀቂያ ካስገቡ በኋላ ጥያቄያቸው ተቀባይነት ሲያገኝ ምክንያታቸውን እንደሚገልጹ መግለጫ ሰጥተው ነበር፡፡ ከዚያም ኃላፊነታቸውን የለቀቁት የድርጅታቸው ኦሕዴድ እና የሕዝባቸው ክብር በመነካቱ መሆኑን መግለጻቸው ይታወሳል፡፡ በቅርቡም ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም የአፈ ጉባዔው የሥራ የመልቀቂያ ጥያቄ ላይ እየተደራደሩ መሆናቸውን መዘገባችን ይታወሳል፡፡