Widgetized Section

Go to Admin » Appearance » Widgets » and move Gabfire Widget: Social into that MastheadOverlay zone

ለአማራና ትግራይ ህዝቦች የምክክር መድረክ ተሳታፊዎች ጎንደር ገብተዋል


አዲስ አበባ፣ ህዳር 8፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) በነገው እለት በጎንደር ከተማ የአማራና የትግራይ ክልል የሃገር ሽማግሌዎች የሚሳተፉበትን የሰላም ኮንፈረንስ ለማካሄድ አስፈላጊውን ዝግጅት ማጠናቀቁን የአማራ ክልል አስታወቀ።

ለአማራና ትግራይ ህዝቦች የምክክር መድረክ ተሳታፊዎችም ጎንደር ገብተዋል።
የአማራና የትግራይ የሀገር ሽማግሌ ተወካዮች ኮንፍረንሱን በማስመልከት በጋራ በሰጡት መግለጫ ኮንፍረንሱን ለማካሄድ ቅድመ ዝግጅት መጠናቀቁን አስታውቀዋል።

የአማራ ክልል የሀገር ሽማግሌ ተወካይ አቶ ሞላ መኮነን፥ በነገው እለት የሁለቱ እህትማማች ህዝቦች ግንኙነት ለማጠናከር ለሚካሄደው ኮንፈረንስ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች ተጠናቀዋል ብለዋል።

የሁለቱን ህዝቦች ግንኙነት ለማጠናከር ተከታታይ የህዝብ ኮንፈረሶችም በቀጣይ ይደረጋሉ ሲሉም አቶ ሞላ መኮነን ተናግረዋል።

የትግራይ ክልል የሀገር ሽማግሌ ተወካይ አቶ መላከ ፀሀይ ገብረ ሚካኤል በበኩላቸው፥ በሁለቱ ህዝቦች የቆየውን ግንኙነት ለማጠናከር ባለፈው ዓመት መቀሌ ላይ በተካሄደው ኮንፈረስ የተሻለ ውጤት መጥቷል ብለዋል።

የክልሉ መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ሃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንዳሉት፥ የሰላም ኮንፈረንሱን በተሳካ ሁኔታ ለማካሄድ ዝግጅት ተጠናቋል።

አቶ ንጉሱ ባለፈው ሃምሌ ወር ላይ በመቐለ ከተማ በተካሄደው የሁለቱ ክልል ህዝቦች የሰላም ኮንፈረንስ ግብዓት የሚሆኑ ሃሳቦች መገኘታቸውን አስታውሰዋል።

ከነገ ጀምሮ ለሁለት ቀናት የሚቆየው የሰላም ኮንፈረንስም የሁለቱን ክልሎች የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ማጠናከርን መሰረት ያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

ከዚህ ባለፈም የክልሎቹ ጉርብትና ሰላማዊና የተረጋጋ እንዲሆን በሚያግዝ መልኩ ይካሄዳልም ነው ያሉት።

በሁለቱ ክልሎች መካከል ያለውን የጋራ መተሳሰብና ወዳጅነት ለመፍጠርም ነገ የሚጀመረው የሰላም ኮንፈረንስ ትልቅ አቅም ይሆናል ብለዋል።

ኮንፈረንሱ ግንኙነትን በማጠናከር ስጋቶችን ለመለየትና አማራጮችን ለማስቀመጥ እንደሚረዳም አንስተዋል።

በተጨማሪም ለዘመናት የቆየውን የሁለቱን ክልሎች የህዝብ ለህዝብ ትብብር በማዳበር ወንድማማችነትን እንደሚያጠናክርም አስረድተዋል።

ኮንፈረንሱ በሁለቱ ክልሎች የሰፈነውን ሰላም ቀጣይነት የማረጋገጥ አላማ ያለው ሲሆን፥ ከሁለቱም ክልሎች ከ1 ሺህ 300 በላይ የሃገር ሽማግሌዎች፣ ምሁራንና የህዝብ ተወካዮች ይሳተፉበታል ተብሎ ይጠበቃል።

የመድረኩ ተሳታፊዎች ጎንደር የገቡ ሲሆን፥ በዚሁ ወቅት ደማቅ አቀባበል ተደርጎላቸዋል።

በነገው እለት በሚካሄደው የትግራይና የአማራ ህዝብ ለህዝብ ኮንፈረስ በሁለቱም ክልሎች በኩል ከ1 ሺ 200 ህዝብ በላይ ይሳተፋል ተብሎ ይጠበቃል።