Widgetized Section

Go to Admin » Appearance » Widgets » and move Gabfire Widget: Social into that MastheadOverlay zone

የአሜሪካ፣ ካናዳ፣ ጃፓንና ሜክሲኮ አምባሳደሮች የሕዳሴውን ግድብ ጎበኙ


አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 21፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ የአሜሪካ፣ ካናዳ፣ ጃፓንና ሜክሲኮ አምበሳደሮች ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታን ጎበኙ።

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሀገሪቱ ከሌሎች ሀገራት ጋር ያላትን የኢኮኖሚ ትስስር የሚያሳድግ መሆኑን፥ አምባሳደሮቹ ገልፀዋል።

የህዳሴው ግድብ ፕሮጀክት የጋራ ተጠቃሚነትን መሰረት ያደረገ እንዲሁም የተፋሰሱ ሀገራትን ምክንያታዊና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ከግምት ያስገባ መሆኑን አምባሳደሮቹ ከጉብኝቱ በኋላ ተናግረዋል።

የአራቱም የበለፀጉ ሀገራት አምባሳደሮች በጉብኝታቸው የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት ቁርጠኝነት ሀገሪቱን በቀጠናው የኤሌትሪክ ኃይል ማዕከል ወደ መሆን እያሸጋገራት ነው በማለት አድናቆታቸውን ገልጸዋል።

ለህብረተሰቡ ኑሮ መለወጥ ኤሌክትሪክ ኃይል ወሳኝ ሚና እንደሚጫወት የገለጹት አምበሳደሮቹ፥ የህዳሴው ግድብ በዚሁ ረገድ ትልቅ አስተዋፅኦ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ የካናዳ አምባሳደር ፊሊፕ ቤከር ላለፉት ዓመታት በሀገሪቱ ህዝብ ተሳትፎ እየተገነባ ያለውን ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለመጎብኘት ሲመኙ መቆየታቸውንና በጉብኝቱ መደሰታቸውን ገልጸዋል።

የህዳሴ ግድብ ግንባታ የሚደነቅ የምህንድና ጥበብ እና ሀገራዊ ስሜት የሚታይበት መሆኑን የተናገሩት ደግም፥ በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምበሳደር ሚካኤል ራይኖር ናቸው።

የኃይል ዕጥረት መሰረታዊ የልማት ፈተና መሆኑን የተናገሩት አምባሳደሩ “ግድቡ ሀገሪቷን ከጎረቤት አገሮች ጋር የሚያስተሳር ነው” ሲሉም ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ የሜክሲኮ አምባሳደር ቪክቶር ትሬቪኖ፥ የህዳሴ ግድቡ ኃይል ከማመንጨት ባሻገር በአካባቢው ትልቅ የቱሪዝም ማዕከል እንደሚሆን ጠቁመው፥ በቱሪዝም ዘርፍ ሀገራቸው ልምድ ለማካፈልና ለመተባበር እንደምትፈልግም ተናግረዋል።

የፕሮጀክቱ ዋና ሥራ አስከያጅ ኢንጅነር ስመኘው በቀለ፥ ግድቡ ውሃ ሳያባክን የተፋሰሱ ሀገራት ከዚህ ቀደም ከነበረው ፍሰት የበለጠና የተሻለ ውሃ ዓመት ሙሉ እንዲያገኙ እንደሚያደርግ ለአምበሳደሮቹ አስረድተዋል።

ኢንጅነሩ እንዳስረዱት ግድቡ የጋራ ተጠቃሚነትን መሰረት የሚያረጋገጥና ለዘመናት የዘለቀውን የተፋሰሱ አገሮች የተሳሳተ አረዳድ በማስወገድ አዲስ የትብብር ምዕራፍ የሚከፍት ነው።

የበለፀጉ ሀገራት አምባሳደሮች ያደረጉት ጉብኝት በኢትዮጵያ እየተሰራ ያለውን ግድብ ሁለንትናዊ ጠቀሜታ ለማሳየት ያግዘናል ነው ያሉት።