Widgetized Section

Go to Admin » Appearance » Widgets » and move Gabfire Widget: Social into that MastheadOverlay zone

ቤተ ክህነት ባለድርሻ የሆነችበት ባንክ ሊመሠረት መሆኑ ተሰማ

መመሥረቻ ካፒታሉ 2.2 ቢሊዮን ብር ነው ተብሏል
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን (ቤተ ክህነት) ባለድርሻ የሆነችበትና ተጨማሪ 18 ባለድርሻዎች የተካተቱበት ባንክ ለመመሥረት ቅድመ ሁኔታዎች መጠናቀቃቸው ተሰማ፡፡

ከሁለት ዓመት በፊት ባንኩን ለመመሥረት ከፍተኛ አማካሪዎች ሁኔታዎችን ሲያመቻቹና የአመሠራረቱ ሁኔታ በልዩ ሚስጥር ሲካሄድ ቆይቶ፣ የድርሻው መጠንና የመሥራቾች ብዛት መወሰኑን ምንጮች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ በዚህም መሠረት አዲስ የሚመሠረተው ባንክ ባለድርሻዎች ብዛት 22 ሲሆን፣ እያንዳንዱ ባለድርሻ አንድ መቶ ሚሊዮን ብር ድርሻ እንዲኖረውና ጠቅላላ መመሥረቻ ካፒታሉ 2.2 ቢሊዮን ብር እንዲሆን ውሳኔ ላይ መደረሱንም ምንጮች አረጋግጠዋል፡፡

ቤተ ክህነት በተለያዩ የልማት ሥራዎች ላይ ባሉ አራት ድርጅቶች አማካይነት የአራት መቶ ሚሊዮን ብር ድርሻ የሚኖራት ሲሆን፣ ቀሪዎቹ 18 ባለድርሻዎች ደግሞ የአንድ ቢሊዮን ስምንት መቶ ሚሊዮን ብር ድርሻ ይኖራቸዋል፡፡ ባለድርሻዎቹ ለምሥረታው 25 በመቶ ቅድሚያ ክፍያ ፈጽመው፣ ቀሪውን ወደፊት በሚወሰነው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት እንደሚከፍሉም ተጠቁሟል፡፡

ቤተ ክህነት ከምዕመኖቿ የምትሰበስበው ገንዘብ ከፍተኛ በመሆኑ ምክንያት፣ ገንዘቡን በባንክ ከማስቀመጥ ይልቅ በአዲስ በሚቋቋመው ባንክ ባለድርሻ መሆኗ የተሻለ ተጠቃሚ ሊያደርጋት እንደሚችል የኢንዱስትሪው ባለሙያዎች ገልጸዋል፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በከፍተኛ ሁኔታ በሚቆጣጠረው የፋይናንስ ሴክተር ውስጥ ያሉት የአገሪቷ ባንኮች በየዓመቱ ከፍተኛ ትርፍ እያስመዘገቡ ይገኛሉ፡፡

ብሔራዊ ባንክ ባወጣው መመርያ መሠረት የባንክ መመሥረቻ የተከፈለ ካፒታል 500 ሚሊዮን ብር በላይ ሲሆን፣ አዲስ የሚመሠረተው ባንክም ይህንኑ መመርያ ተግባራዊ የሚያደርግ ይሆናል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ማብቂያ ላይ የባንክ መመሥረቻ የተከፈለ ካፒታል ወደ ሁለት ቢሊዮን ብር ያድጋል በመባሉ፣ በሥራ ላይ ያሉት ባንኮች ይኼንን ማሟላት ካልቻሉ ወደ ውህደት የሚሄዱበት አቅጣጫ በብሔራዊ ባንክ ተቀምጧል፡፡

ይህ መመርያ ከወጣ በኋላ በምሥረታ ላይ የነበሩ ባንኮች የፈረሱ ሲሆን፣ አዲስ የሚቋቋመው ባንክ ይህን መመርያ ተቋቁሞ ወደ ምሥረታ መቃረቡ ከፍተኛ የገንዘብ አቅም እንዳለው ማሳያ መሆኑንም አስተያየት ሰጪዎች ተናግረዋል፡፡

የባንኩን ስያሜ በሚመለከት ‹‹ዳሎል›› ወይም ‹‹ሰላም›› ባንክ ይባል በሚባለው ላይ ቅዳሜ መስከረም 27 ቀን 2010 ዓ.ም. ውሳኔ ላይ እንደሚደረስ ምንጮች ተናግረዋል፡፡

ያለምንም ሕዝባዊ ማስታወቂያ በልዩ ሚስጥር እንዲመሠረት የተደረገው ባንክ አክሲዮን ሽያጭ ማክሰኞ መስከረም 30 ቀን 2010 ዓ.ም. እንደሚጠናቀቅም ተጠቁሟል፡፡
Source:Ethiopian Reporter