Widgetized Section

Go to Admin » Appearance » Widgets » and move Gabfire Widget: Social into that MastheadOverlay zone

የአገሪቷ ደካማ የሚዲያና የህዝብ ግንኙነት ስራ ዋጋ እያስከፈለ ነው


አዲስ አበባ ሚያዚያ 28/2009 የተሻለ አፈጻጸም የተመዘገበባቸው አገራዊ ስኬቶች ቢኖሩም የሚዲያና የህዝብ ግንኙነት ስራዎች ደካማ መሆን ዋጋ እያስከፈለ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ተናገሩ።

የሚዲያና የህዝብ ግንኙነት ዘርፍ ሚኒስትሮች፣ የክልል ርዕሰ መስተዳድሮች፣ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊዎች፣ የመገናኛ ብዙሃን መሪዎች፣ ምሁራንና ባለድርሻ አካላት የተሳተፉበት አገራዊ የምክክር መድረክ በአዲስ አበባ ተካሂዷል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም በውይይቱ ላይ በአገሪቷ የተለያዩ አካባቢዎች በህዝቡና በየደረጃው በሚገኙ ተቋማት የተሰሩ መልካም አፈጻጸሞች ቢኖሩም ሚዲያውና የህዝብ ግንኙነት ተቋማት በሚጠበቀው ልክ እየሰሩ እንዳልሆነ ነው የተናገሩት።

የሚዲያና የህዝብ ግንኙነት ተቋማት ኃላፊዎች በበኩላቸው አገራዊ የህዝብ ግንኙነት ስራው የሚፈለገውን ውጤት ላለማምጣቱ ወጥ የህዝብ ግንኙነት አሰራር አለመዘርጋት፣ የመገናኛ ብዙሃንና የመንግስት ተቋማት ህዝብ ግንኙነት ሃላፊዎች አለመግባባትና የአቅም ውስንነትን በምክንያትነት አንስተዋል።

“የህዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች የተቋማቸውን ዓቢይ ተልዕኮ በመረዳት ትክክለኛና ወቅታዊ መረጃ ለህብረተሰቡ በፍጥነት ተደራሽ ማድረግ አለባቸው” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ለስራቸው እንቅፋት የሆኑ አሰራሮችን እንዲፈታ አሳስበዋል።

ሁሉም የመንግስት የስራ ኃላፊዎች የመጀመሪያው የተቋማቸው የህዝብ ግንኙነት ሊሆኑ እንደሚገባና የመረጃ ጥያቄ ከመገናኛ ብዙሃን፣ ከግለሰቦች ወይም ከሌሎች ተቋማት ሲቀርብላቸው ወቅታዊ ምላሽ መስጠት እንዳለባቸውም አስገነዝበዋል።

የመረጃ ነጻነት አዋጅ አተገባበርን በሚመለከት አዋጁን ሙሉ ለሙሉ መተግበር የሚያስችሉ የህግ ማዕቀፎች አለመዘጋጀት፣ የተቋማት የተደራጀ የመረጃ ማዕከል አለመኖር፣ የሰነድ ስራ አመራር ስርዓት አለመዘርጋት፣ ለህዝብ ይፋ መደረግ ያለበትን መረጃ ሚስጥር ማድረግና መሰል ችግሮች አሁንም መቀጠላቸው በውይይቱ ወቅት ተገምግሟል።