Widgetized Section

Go to Admin » Appearance » Widgets » and move Gabfire Widget: Social into that MastheadOverlay zone

16ኛው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ተካሄደ

img_2250
አዲስ አበባ፣ ህዳር 11፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) 16ኛው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ዛሬ ተካሂዷል።

መነሻና መድረሻውን መስቀል አደባባይ አድርጎ በተካሄደው የዘንድሮ ታላቁ ሩጫ ውድድር ላይ 42 ሺህ ሰዎች ተሳታፊ ሆነዋል።

ከዚህ በተጨማሪም በ2009 የቶታል ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ 500 አትሌቶች የተወዳደሩ ሲሆን፥ ሁለት ኬንያዊያን አትሌቶችም ተሳትፈዋል።

በዚህም መሰረት የ10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫውን በወንዶች አትሌት አቤ ጋሻሁን ከአማራ ማረሚያ ቤት አንደኛ በመሆን አጠናቋል።

አትሌት አቤ ጋሻሁን ውድድሩን ለመጨረስ 28 ደቂቃ 53 ሴኮንድ ከ 80 ማይክሮ ሴኮንድ ፈጅቶበታል።

እንዲሁም ኬንያዊው አትሌት ጆሩም ሉምባሲ ሁለተኛ የወጣ ሲሆን፥ አትሌት አዱኛ ታከለ ከኦሮሚያ ፖሊስ ሶስተኛ በመሆን ውድድሩን አጠናቋል።

በሴቶች በተደረገ ውድድርም አትሌት ፎቴን ተስፋዬ ከመሰቦ ስፖርት ክለብ አንደኛ መበሆን ውድድሯን አጠናቃለች።

ፎቴን ተስፋዬ በ33 ደቂቃ ከ 09 ሴኮንድ በመግባት አሸናፊ ሆናለች።

እንዲሁም አትሌት ሙልዬ ደቀቦ ከኦሮሚያ ፖሊስ ሁለተኛ በመሆን ውድድሩን ያጠናቀቀች ሲሆን፥ አትሌት ታደለች በቀለ ከኦሮሚያ ማረሚያ ቤት ሶስተኛ በመውጣት ውድድሯን አጠናቃለች።

በውድድሩ ላይ ከአንድ እስከ ሶስት ለወጡ ለሁሉም አትሌቶች የዋንጫ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

ከዚህ በተጨማሪም በወንዶች እና በሴቶች ውድድሩን አንደኛ በመውጣት ላጠናቀቁ አትሌቶች የ50 ሺህ ብር ሽልማት ተሰጥቷል።

እንዲሁም ሁለተኛ ለወጡ 25 ሺህ ሶስተኛ ሆነው ላጠናቀቁ ደግሞ የ 10 ሺህ ብር ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

የዘንድሮ ውድድር በታላቁ ሩጫ ታሪክ ክብረ ወሰን የሆነ 42 ሺህ ሰዎች የተሳተፉበት ሲሆን፥ በዚህ ውድድር የቀይና አረንጓዴ ቲሸርት ለባሾች የተለያየ መነሻዎችን በማድረግ ነው የተካሄደው።

ቀይ ለብሰው የሚሳተፉ ተወዳዳሪዎች ከ1 ሰአት በታች መግባት የሚችሉ ብቻ ሲሆኑ፥ አረንጓዴ የሚለብሱት ከ1 ስአት በላይ የሚገቡት ናቸው።

ከ250 በላይ የውጭ ሃገር ተሳታፊዎች ከ20 በላይ የተለያዩ ሃገራት በውድድሩ ላይ መሳተፋቸውም ተገልጿል።

የአፍሪካ ትልቁ የጎዳና ሩጫ የዘንድሮ ዋና መልዕክት “መኖር ለዚህ አበቃኝ” በሚል ከብሄራዊ የአደጋ ስጋት ቅነሳ ስራ አመራር ኮሚሽን ጋር በመተባበር ተላልፏል።