Widgetized Section

Go to Admin » Appearance » Widgets » and move Gabfire Widget: Social into that MastheadOverlay zone

የጅግጅጋና አከባቢዋ ነዋሪዎች ለህገ መንግሥቱና ለፌዴራል ሥርዓቱ ያላቸውን ድጋፍ ለማሳየት ዛሬ ሰልፍ አካሄዱ

jijigajijiga-2
አዲስ አበባ፣ መስከረም 17፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ህገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ ለመጣል የሚደረጉ ማናቸውንም እንቅስቃሴዎች ከማውገዝ አልፈው በጽናት እንደሚታገሉ በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል የጅግጅጋ ከተማና የፋፈን ዞን ነዋሪዎች አስታወቁ።
ከጅግጅጋ ከተማና ከፋፈን ዞን ወረዳዎች የተውጣጡ በሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች ለህገ መንግሥቱና ለፌዴራሊዝም ሥርዓቱ ያላቸውን ድጋፍ ዛሬ በጅግጅጋ ከተማ ባካሄዱት የድጋፍ ሰልፍ አረጋግጠዋል።
ህገ-መንግሥቱን መሰረት አድርጎ ተግባራዊ የሆነው የፌዴራሊዝም ሥርዓት የሀገሪቱ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶቻቸው ተከብረው በማንነታቸው፣ ባህላቸውና በሃይማኖታቸው እንዲኮሩ፣ በቋንቋቸው እንዲማሩ፣ እንዲዳኙና እንዲሰሩ ያስቻለ መሆኑን ሰለፈኞቹ በዚሁ ጊዜ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ሕዝብም በህገ-መንግሥቱ በተረጋገጠው የፌዴራሊዝም ሥርዓት ባገኘው ራስን በራስ የማስተዳደር መብት ተጠቅሞ በክልሉ ልማት ቀጥተኛ ተሳታፊና ተጠቃሚ መሆኑንም አረጋግጠዋል።
የግብርና፣ የጤና፣ የትምህርት፣ የንጹህ መጠጥ ውሃና የመሰረተ ልማት አውታሮችን ጨምሮ የዘርፈ ብዙ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ውጤቶች ተጠቃሚ መሆናቸውንም ተናግረዋል።
የፌዴራሊዝም ሥርዓቱ ከሌሎች የሀገሪቱ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ጋር ተከባብረው፣ ተቻችለውና ተፈቃቅደው በአንድነት እንዲኖሩ ያስቻለ መሆኑንም አመልክተዋል።
በመሆኑም ህገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ ለመጣል የሚደረጉ ማናቸውንም እንቅስቃሴዎች ከማውገዝ ባሻገር ከመንግሥት ጎን ሆነው በጽናት ለመታገል ዝግጁ መሆናቸውን በድጋፍ ሰልፉ አረጋግጠዋል።
ሰልፈኞቹ ከያዟቸው መፈክሮች መካከል “የብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ሰብዓዊም ሆነ ዲሞክራሲያዊ መብቶች ያረጋገጠውን ህግ መንግሥት ለመሸራረፍ መሞከር ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓታችንን መዳፈር በመሆኑ የህይወት ዋጋ እንከፍላለን፣ ግንቦት7 ኦነግ እና ኦብነግ ፀረ ሰላም ኃይሎች የፌዴራሊዝም ስርዓታችንና የአንድነታችን ጠላቶች ናቸው፤ ህግ መንግሥታችንን ከማንኛውም ጠላት ለመከላከል ተዘጋጅተናል” የሚሉት ይገኙበታል።
የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አቶ አብዲ መሀሙድ በዚሁ ጊዜ ባደረጉት ንግግር በኢህአዴግና አጋር ድርጅቶቹ ባለፉት 15 ዓመታት የሀገራችንን ህዝቦች ከድህነት ለማላቀቅ በርካታ ስኬታማ ስራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል።
ርዕሰ መስተዳደሩ አያይዘውም በአሁኑ ወቅት ፀረ ሰላም ኃይሎች የቀድሞውን ጭቋኝ ሥርዓት ለመመለስ የተለያዩ አፍራሽ እንቅሰቃሴዎችን እያደረጉ መሆናቸውን ጠቁመው፥ ይህን እኩይ ተግባራቸውን ህዝቡ ለአፍታም መታገስ እንደማይችል አስረድተዋል።
በድጋፍ ሰልፉ በሺዎች የሚቆጠሩ የጅግጅጋ ከተማ፣ የአውበሬ፣ ቀብሪበያህ፣ ቱሊጉሌድ፣ ጉርሱምና ጅግጅጋ ወረዳ ነዋሪዎች መሳተፋቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

jijiga-3