Widgetized Section

Go to Admin » Appearance » Widgets » and move Gabfire Widget: Social into that MastheadOverlay zone

የአሜሪካ የኮንግረስ አባላት በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ላይ ያነጣጠረ ረቂቅ ውሳኔ አቀረቡ; ‹‹ረቂቁ እንደ ኢንፍሉዌንዛ ጊዜ እየጠበቀ የሚወጣ ነው›› አቶ ጌታቸው ረዳ

getache-reda
የአሜሪካ ሕግ አውጪ ምክር ቤት በያዝነው ሳምንት በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት አያያዝ ላይ የቀረበለትን ረቂቅ ውሳኔ መንግሥት አጣጣለው፡፡ በአፍሪካ ጉዳዮች ንዑስ ቋሚ ኮሚቴ ሊቀመንበር ክሪስ ስሚዝ የቀረበውና “HR 2016” የተባለው ረቂቅ፣ በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት እንዲከበር የሚጠይቅና የታሰሩ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎችና ጋዜጠኞች በአስቸኳይ እንዲለቀቁ ይጠይቃል፡፡ ረቂቁ በአገሪቱ ተቃውሞ የሚያደርጉ ዜጎች ላይ የፀጥታ ኃይሎች የሚወስዱትን የኃይል ዕርምጃ በመኮነን፣ በአማራና በኦሮሚያ በፀጥታ ኃይሎች ስለተገደሉት ሰዎች ተዓማኒነት ያለው ምርመራ እንዲካሄድ ጠይቋል፡፡ በተጨማሪም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በኢትዮጵያ ስላለው የሰብዓዊ መብት አያያዝ ምርመራ አድርጎ ሪፖርት እንዲያቀርብ ጠይቋል፡፡
 
የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጌታቸው ረዳ፣ ‹‹ይህ እንደ ኢንፍሉዌንዛ ጊዜ እየጠበቀ የሚወጣና ዴሞክራሲ ከአሜሪካ ብቻ ነው የሚመጣው የሚል አመለካከትን የሚያንፀባርቅ ነው፤›› ብለዋል፡፡ ረቂቁን በመሪነት ያቀረቡት ክሪስ ስሚዝ ለበርካታ ዓመታት በኢትዮጵያ ላይ ተመሳሳይ ረቂቆችን ለማቅረብ ሲጣጣሩ የቆዩ ግለሰብ መሆናቸውን የገለጹት አቶ ጌታቸው፣ የኢትዮጵያ ዴሞክራሲ ከአሜሪካ ተነስቶ ሊበለጽግ እንደማይችል ተናግረዋል፡፡ በአገሪቱ ለተፈጠረው ችግር መፍትሔ መምጣት ያለበት ከኢትዮጵያ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
አዲሱ ረቂቅ እ.ኤ.አ. መጋቢት 2016 በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኤምባሲ ፊት ለፊት ተቃውሞ ያሰሙ 20 የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች መታሰራቸው፣ የኦሮሚያ ፌዴራሊስት ኮንግረስ ምክትል ሊቀመንበር አቶ በቀለ ገርባንና ሌሎች 21 የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች በፀረ ሽብር ሕጉ መታሰራቸው፣ እንዲሁም ሌሎች ጋዜጠኞችና ብሎገሮች በአሸባሪነት በመከሰሳቸው ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የሰብዓዊ መብት ችግር ያሳያል ይላል፡፡ ረቂቁ በቅርቡ በቂሊንጦ እስር ቤት ላይ የደረሰው ቃጠሎ ተመርምሮ ለሕዝብ እንዲገለጽ ጠይቆ፣ ሰላማዊ ሠልፈኞችና ተቃዋሚዎች የመናገርና የመቃወም መብታቸው እንዲጠበቅላቸው ይጠይቃል፡፡ በመሆኑም የአሜሪካ መንግሥት ለኢትዮጵያ የሚያደርገውን የደኅንነት ዕርዳታ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ በድጋሚ እንዲያጠናው ጠይቋል፡፡ የአሜሪካ ሕግ አውጪ ምክር ቤት ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጎን እንደሚቆም ገልጾ፣ በሕገ መንግሥቱ የተቀመጡ መብቶችና ዴሞክራሲያዊ ምኅዳሩ እንዲሰፋ ጠይቋል፡፡
ከዚህ ቀደም ከምርጫ 97 በኋላ ለአሜሪካ ሕግ አውጪ ምክር ቤት የቀረበው “HR 2003” ረቂቅ ሕግ ሆኖ እንዳይፀድቅ የኢትዮጵያ መንግሥት በበርካታ ሚሊዮን ዶላሮች ወትዋች ቡድን (Lobby Group) ቀጥሮ ረቂቁ ሕግ ከመሆን አስቀርቶታል፡፡ አቶ ጌታቸው ለአዲሱ ረቂቅ ምንም ዓይነት ወትዋች ቡድን መንግሥት እንደማይቀጥር ገልጸዋል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥትን የሚደግፉ በርካታ የአሜሪካ ባለሥልጣናት ስላሉ፣ መንግሥት ተጨማሪ ወትዋቾች እንደማያስፈልጉትም ተናግረዋል፡፡
በአገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች በተለይም በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች በተነሱ ተቃውሞዎች የበርካታ ዜጎች ሕይወት ማለፉና ንብረት መውደም ተከትሎ የአሜሪካ ባለሥልጣናት የተለያዩ መግለጫዎች እያወጡ ይገኛሉ፡፡ እነዚህን መግለጫዎች ባያወጡ ጥሩ መሆኑን የገለጹት አቶ ጌታቸው፣ የሁለቱ መንግሥታት ግንኙነት ግን በጋራ ጥቅም ላይ የተመሠረተ በመሆኑ መግለጫዎቹ ግንኙነቱን እንደሚያሻክሩት ገልጸዋል፡፡
በኮንግረስ ክሪስ ስሚዝ መሪነትና በሌሎች የኮንግረስ አባላት ረቂቁ ለአሜሪካ ሕግ አውጪ ምክር ቤት በቀረበበት ወቅት፣ በቅርቡ በሪዮ ኦሊምፒክ የብር ሜዳሊያ ያገኘውና ተቃውሞውን በዓለም አቀፍ መድረክ ያሳየው አትሌት ሌሊሳ ፈይሳን ጨምሮ በርካታ ኢትዮጵያዊያን ተገኝተዋል፡፡

One Response to የአሜሪካ የኮንግረስ አባላት በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ላይ ያነጣጠረ ረቂቅ ውሳኔ አቀረቡ; ‹‹ረቂቁ እንደ ኢንፍሉዌንዛ ጊዜ እየጠበቀ የሚወጣ ነው›› አቶ ጌታቸው ረዳ