Widgetized Section

Go to Admin » Appearance » Widgets » and move Gabfire Widget: Social into that MastheadOverlay zone

ታራሚዎችን ጉቦ በመቀበል ነፃ እንዲወጡ ያደረጉ የፍርድ ቤት ፕሬዚዳንትና ዳኛ በእስራት ተቀጡ

court-of-law
አዲስ አበባ ፣ መስከረም 11 ፣ 2009 (ኤፍ ቢ ሲ) 3 ዓመት ከ6 ወር የተፈረደባቸውን 2 ተከሳሾች በ29 ሺህ ብር ነፃ እንዲወጡ ያደረጉ የፍርድ ቤት ፕሬዚዳንትና ዳኛ ከ3 ዓመት እስከ 6 ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራትና በገንዘብ ተቀጡ።
የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ክስ የመሰረተባቸው 1ኛ ተከሳሽ ዮሐንስ ገብረመድህን በትግራይ ክልል የሰሜናዊ ምዕራብ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት 2ኛ ተከሳሽ ሃጎስ አብርሃም ደግሞ በፍርድ ቤቱ ዳኛ የነበረ ነው።
ሁለት ወንድማማቶች በ2008 ዓ.ም መጀመሪያ በትግራይ ሰሜን ምዕራባዊ ዞን የሰው አካል በማጉደል ወንጀል ክስ ይመሰረትባቸዋል።
የተመስረተባቸውን ክስ በመረጃ ማስተባበል ሳይችሉ በመቅረቱ ጉዳዩን ሲመረመር የቆየው ፍርድ ቤት ጥፋተኛ በማለት እያንዳንቸው በ3 ዓመት ከ6 ወር ፅኑ እስራት እንዲቀጡ ይወስናል።
1ኛ ተከሳሽ በዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ሆኖ በሚሰራበት ወቅት 2ኛ ተከሳሽ ከሆነው ዳኛ ጋር በማበር መንቀሳቀሳቸው ነው በክሱ የተገለፀው።
1ኛ ተከሳሽ ፍርድ ተሰጥቷቸው በማረሚያ ቤት የሚገኙ ሁለት ወንድሞቹ ነፃ እንዲወጡ እንደሚያደርግ የታራሚዎቹ ሶስተኛ ወንድም ይናገራል።
ይህ ተግባርም በእሱና በፍርድ ቤቱ በሚገኝ ሌላ ዳኛ እንደሚፈፀም በማስረዳት ለዚህ ተግባራቸው ይገባናል የሚሉትን እጅ መንሻ በመደራደሪያነት ያቀርባል።
በጥሬ ገንዘብ 29 ሺህ ብር፣ ላፕቶፕ ኮምፒዩተርና 3 ሺህ 5 መቶ ብር የሚያወጣ ተንቀሳቃሽ ስልክን፥ ሁለቱን ወንድማማቾች ነፃ ለማውጣት ቅድመ ሁኔታ ሆኖ ቀርቧል።
ወንድሞቹ ከማረሚያ ቤት እንዲወጡለት ከፈለገው ወንድም 29 ሺህ ብርና ተንቀሳቃሽ ስልኩን ሁለቱ ተከሳሾች መቀበላቸውንም በክሱ ተጠቅሷል።
ይህ መደለያ የቀረበላቸው የፍርድ ቤት ፕሬዚዳንትና ዳኛ፥ በተደጋጋሚ ከስልጣናቸው ውጪ የማይገባቸውን የሌሎች የችሎት ጉዳዮችን በመመልከት ሁለት ወንድማማች ታራሚዎችን ነፃ እንዲወጡ አድርገዋል።
በዚህም ጠቅላይ አቃቢ ህግ ጉቦ የመቀበልና ስልጣንን ያለአግባብ መጠቀም የሙስና ወንጀል ክሶችን፥ የቀድሞ የፍርድ ቤት ፕሬዚዳንትና ዳኛ ሆነው ሲያገለግሉ በቆዩት ሁለት ግለሰቦች ላይ መስርቶባቸዋል።
ተከሳሾቹ ቀድሞ ይሰሩበት በነበረው ሺሬ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቀርበው ክሱ በዝርዝር ቢነበብላቸውም የወንጀል ድርጊቱን አልፈፀምንም በማለት የእምነት ክህደት ቃላቸውን ሰጥተዋል።
ጠቅላይ አቃቢ ህግም የሰውና የሰነድ ማስረጃዎችን ለፍርድ ቤት በማቅረብ የወንጀል ድርጊቱ በሁለቱ ግለሰቦች ስለመፈፀሙ አስረድቷል።
ተከሳሾቹ የቀረበባቸውን ክስ ማስተባበል ባለመቻላቸውም የሺሬ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሁለቱን ተከሳሾች ጥፋተኛ ብሏቸዋል።
ፈርድ ቤቱም ተከሳሾች ያቀረቡትን የቅጣት ማቅለያና የጠቅላይ አቃቢ ህግ የቅጣት ማክበጃ በመያዝ፥ 1ኛ ተከሳሽን በወንጀል ድርጊቱ የነበረው ተሳትፎ ከፍተኛ በመሆኑ በ6 ዓመት ፅኑ እስራትና በ5 ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት እንዲሁም፥ 2ኛ ተከሳሽን ደግሞ በ3 ዓመት ፅኑ እስራትና በ1 ሺህ ብር እንዲቀጣ ፍርድ ቤቱ ውሳኔውን አስተላልፏል።