Widgetized Section

Go to Admin » Appearance » Widgets » and move Gabfire Widget: Social into that MastheadOverlay zone

በአማራ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች የተከሰተውን ሁከት ተከትሎ መንግስት ከህዝቡ ጋር እየተወያየ ነው

nuguse tilahun
አዲስ አበባ ፣ ነሃሴ 27 ፣ 2008 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች የተከሰተውን ሁከት ተከትሎ መንግስት የማረጋጋት ስራውን አጠናክሮ መቀጠሉን የክልሉ ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ ንጉሱ ጥላሁን ተናገሩ።

በክልሉ ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ዜና መጽሄት ጋር ቆይታ ያደረጉት ዋና ዳይሬክተሩ፥ በክልሉ በተለይም በምዕራቡ አካባቢ ሁከት መከሰቱን ተናግረዋል።

በአንዳንድ ፀረ ሰላም ሃይሎች በማህበራዊ ትስስር ገጾች የሚለቀቀው የሃሰት መረጃ ህዝቡን ወዳልተፈለገ አቅጣጫ እየመራው መሆኑንም ነው የተናገሩት።

እነዚህ ሃይሎች የቀረቡ የህዝብ ጥያቄዎችን ተንተርሰው፥ ሁከትና ብጥብጥ በማስነሳት የክልሉን ልማት ለማደናቀፍ እየሰሩ መሆናቸውንም ገልጸዋል።

ዋና ዳይሬክተሩ በተፈጠረው ሁከት በሰው ህይዎትና ንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደርሷል ብለዋል።

በባህርድ ዳር አቅራቢያ የሚገኘው የአበባ እርሻ ልማት ድርጅትና የከተማው የውሃ ማጠራቀሚያ ላይ ጥቃት መሰንዘሩንም አንስተዋል።

በተጨማሪም የጤና ተቋማት ንብረት በሆኑ የአምቡላንስ ተሽከርካሪዎች ላይ ጉዳት መድረሱንም ጠቅሰዋል።

ከዚህ ባለፈም በክልሉ የተለያዩ ከተሞች የስራ ማቆም አድማ በመጥራት ህዝቡን ከዕለት ተዕለት እንቅስቃሴው ለማስተጓጎል ተሞክሯልም ነው ያሉት።

በዚህ ሳቢያም በአንዳንድ ከተሞች የስራ ማቆም አድማ በማያደርጉ የህዝብ መገልገያ ተቋማትና ግለሰቦች ላይ እነዚህ ሃይሎች፥ ሃይል የተቀላቀለበት እርምጃ ወስደዋልም ብለዋል።

ይህን መሰሉ እንቅስቃሴ ፀረ ዴሞክራሲያዊና ፀረ ሰላም መሆኑን ጠቅሰው፥ ድርጊቱ ህዝቡን በሰላም ወጥቶ የመግባት መብቱን መንፈግ እንደሆነም አስረድተዋል።

አቶ ንጉሱ እንዳሉት መንግስት ህግና ስርዓትን ከማስከበር ባለፈ፥ መድረክ በማዘጋጀት ከህዝቡ ጋር እየተወያየ ነው።

በዚህም በአንዳንድ ከተሞች የመንግስት የስራ አመራሮች ከነዋሪዎቹ ጋር የሰላም መድረክ በማዘጋጀት እየተወያዩ መሆኑን ተናግረዋል።

መድረኩ ህዝቡ የሚያነሳቸውን ጥያቄዎች በሰላም እና በውይይት መፍታት የሚችልበትን አግባብ ማመቻቸት አላማ እንዳለውም አስረድተዋል።

በእስካሁኑ የውይይት መድረክም ህዝቡ የጥፋት ሃይሎችን ድርጊት በመቃወም ከመንግስት ጎን መቆሙን ማሳየቱንም ነው ያነሱት።

ውይይቱ ቀጣይነት እንዳለው የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ፥ ከዚህ ጎን ለጎን ጥፋት እንዲደርስ የሚመሩ ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር በማዋል ለፍርድ የማቅረቡ ሂደት መቀጠሉን አውስተዋል።