Widgetized Section

Go to Admin » Appearance » Widgets » and move Gabfire Widget: Social into that MastheadOverlay zone

ከ2 ሺህ 400 ኪ.ሜ በላይ የባቡር መስመሮችን መገንባት የሚያስችል የአዋጭነት ጥናት እየተካሄደ ነው

አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 23፣ 2008 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በሀገር አቀፍ ደረጃ ከ2 ሺህ 400 ኪሎ ሜትር በላይ የባቡር መስመሮችን ለመገንባት የሚያስችል የአዋጭነት ጥናት እየተካሄደ ነው።

የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ግንባታ ምእራፍ ሁለት ግንባታን ጨምሮ ሌሎች የሀገር አቋራጭ መስመሮችን ለማስጀመር የሚያስችል ገንዘብ ማፈላለግ ስራ እያከናወንኩ ነው ብሏል።

ጥናቶቹ ተመዝነው አዋጭ መሆናቸው ሲረጋገጥ አበዳሪ ተቋማት በሚለቁት ገንዘብም ወደ ግንባታ እንደሚገባ ነው ኮርፖሬሽኑ ያስታወቀው።

በሚቀጥሉት ሶስት አመታት ወደ ግንባታ ይገባሉ ተብለው ከሚጠበቁት የባቡር ፕሮጀክቶች ውስጥ ከሞጆ ኮንሶ ሻሸመኔ ሀዋሳ እና አሁን በመገንባት ላይ ካለው የአዋሽ ወልድያ የባቡር መስመር ተነስቶ ባህርዳር የሚገባው የፍኖተሰላም – ባህርዳር – ወሮታ – ወልድያ የባቡር መስመሮች ቀዳሚዎቹ ናቸው።

ከፍኖተ ሰላም ወልድያ የሚገነባው የባቡር መስመር 454 ኪሎ ሜትር ርዝመት የሚኖረው ሲሆን፥ ከሞጆ ተነስቶ በኮንሶ ሻሸመኔ ሀዋሳ የሚገባው የባቡር መስመርም በቀጣይ እስከ ሞያሌ የሚዘረጋ ሆኖ በአጠቃላይ እስከ 950 ኪሎሜትር ርዝመት ይኖረዋል።

ከእነዚህ ዋና ዋና የባቡር መስመሮች በተጨማሪ ከጅማ – ጉራፍርዳ – ዲማ እና ሌሎች ፕሮጀክቶችን ጨምሮ በአጠቃላይ እስከ 2 ሺህ 400 ኪሎ ሜትር የባቡር ፕሮጀክቶች በሶስት አመታት ውሰጥ ግንባታቸው ይጀመራል ተብሎ ይጠበቃል።

የእነዚህን ፕሮጀክቶች የአዋጭነት ጥናት እያጠና ነው፤ ጥናቱ ከተጠናቀቀ በኋላ ፋይናንስ ወደሚያበድሩ ተቋማት በማቅረብና ጥናቱን በማስመዘን ወደ ግንባታ እንደሚገባ የኮርፖሬሽኑ የህዝብ ግንኙነት ክፍል ሃላፊ አቶ ደረጀ ተፈራ ተናግረዋል።

የፕሮጀክቶቹ ግንባታ በብድሩ ግኝት ላይ የተሰመረተ በመሆኑ የግንባታውን መጀመሪያ ጊዜ አሁን ላይ በትክክል መናገር እንደማይቻል ጠቁመዋል።

ያም ሆኖ በቀጣዮቹ ሶስት እና አራት አመታት ሁሉም ፕሮጀክቶች ወደ ግንባታ ይገባሉ ብለዋል አቶ ደረጀ።

እንደየ አዋጭነታቸውም ቀድመው አበዳሪ ያገኙ ፕሮጀክቶች በቅድሚያ ወደ ስራ ይገባሉ ነው ያሉት።

የአዲስ አበባው ቀላል ፕሮጀክት የማስፋፊያ ፕሮጀክትም ከእነዚሁ ሀገር አቀፍ የባቡር መሰረተ ልማት እቅዶች ጋር የሚጓዝ ነው።

በአሁኑ ወቅትም ፕሮጀክቱን ከከተማዋ ማስተር ፕላን ጋር የማቀናጀት ስራ እየተሰራ መሆኑን አቶ ደረጀ ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ በሚቀጥሉት አመታት ግንባታቸው ከሚጀመሩት ፕሮጀክቶች በተጨማሪ በሚቀጥሉት 10 አመታት በደቡብ የሀገሪቱ ክልል ሶዶ አርባምንጭ እና ወይጦ፣ ከሃዋሳ – ሞያሌ – ኢተያ – ኢንደቶ እና ጊኒር በባቡር ፕሮጀክቶች ይተሳሰራሉ።

በሰሜን ምስራቅ ከአዲስ አበባ ደሴ በሁመራ ዴቾ ጋላፊ ድረስ እንዲሁ የባቡር መስመሩ የሚዘረጋባቸው ናቸው።
train