Widgetized Section

Go to Admin » Appearance » Widgets » and move Gabfire Widget: Social into that MastheadOverlay zone

በክልሉ አንዳንድ አካባቢዎች እየተፈጠረ ያለው ሁከትና ግጭት ከዚህ በላይ እንዲቀጥል መንግስት አይፈቀድም – አቶ ገዱ አንዳርጋቸው

gedu
አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 19፣ 2008 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በአማራ ክልል በአንዳንድ አካባቢዎች እየተፈጠረ ያለው ሁከትና ግጭት ከዚህ በላይ እንዲቀጥል መንግስት እንደማይፈቅድ የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ተናገሩ።

ርእሰ መስተዳደሩ ዛሬ በሰጡት መግለጫ እየተፈጠረ ባለው ግጭትና ሁከት መላው ህብረተሰብ ጭንቀትና ፍርሀት እያደረበት ነው፤ ችግሩ ባለባቸው አካባቢዎች በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ላይ ችግር እየተከሰተ ነው ብለዋል።

ይህን ችግር ከዚህ በላይ እንዲቀጥል መፍቀድ ችግሩን የበለጠ ማወሳሰብና በህብረተሰቡና በክልሉ ላይ እየተፈጠረ ያለውን ሰላም የሚያደፈርሰ፤ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችንም ማባባስ በመሆኑ ክልሉ ይህን ማስተካከል የሚያስችል እርምጃ ይወስዳል፤ ለዚህም ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል።

ከሀምሌ ወር መጀመሪያ አንስቶ በጎንደርና አካባቢው በተከሰተው ሁከትና ግጭት በሰው ህይዎትና በንብረት ላይ ከፍተኛ ውድመት መድረሱንም ነው አቶ ገዱ ያነሱት።

ይህ ሁከትና ግጭት በባህር ዳርና አካባቢው ላይም ተከስቶ በሰው ህይወትና ንብረት ላይ ጉዳት መደረሱንም ተናግረዋል።

በክልሉ በአንዳንድ አካባቢዎች የተከሰተው ሁከትና ግጭት ህብረተሰቡ ኑሮ ውስጥ መመሰቃቀል ፈጥሯል ያሉት ርዕሰ መስተዳደሩ፥ ከዚህ በላይ ህብረተሰቡ በፍርሀትና ጭንቀት እንዲሸበበ አድርጓል ብለዋል።

ይህ ሁኔታ እንዲቀጥል ክልሉ አይፈቅድም ያሉት ርዕሰ መስተዳደሩ፥ ይህን ማስተካከል የሚያስችል እርምጃ እንደሚወሰድ አስታውቀዋል።

የዚህ ሁከት መነሻ በህብረተሰቡ ውስጥ የሚነሱ የተለያዩ ጥያቄዎች ናቸው ያሉት አቶ ገዱ፥ ጥያቄዎቹ እየተንከባለሉ መምጠታቸውም አሁን ለደረሰበት በቅቷል ብለዋል።

የክልሉ መንግስት ለሚነሱ ጥያቄዎች እና ሲጓተቱ ለመጡ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት ከሀይማኖት አባቶች፣ ከሀገር ሽማግሌዎችና ከወላጆች፣ ከወጣቶች፣ ከሴቶችና ከሌሎችም የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር ምክክር ማድረጉንም ነው ርዕሰ መስተዳደሩ የገለጹት።

በውይይት መድረኮቹ ከህብረተሰቡ በተነሱ ጉዳዮች ዙሪያ መግባባት ላይ ተደርሷል ያሉት አቶ ገዱ፥ ችግሮቹን ለመፍታት ክልሉ ቁርጠኛ አቋም እንዳለውም አንስተዋል።

ይሁን እንጂ የህዝቡን ጥያቄ በመንጠቅ የራሳቸውን አጀንዳ ማራመድ የሚፈልጉ ፀረ ሰላም አካላት ህዝቡ ውስጥ ያልተገባ ወሬ እየነዙ መሆናቸውንም ተናግረዋል።

ህብረተሰቡ ጸረ ሰላም አካላት በሚነዙ ወሬዎች ሳይደናበር የትኛውንም ጥያቄ በሰላም ማቅረብ እንዳለበትም ርእስ መስተዳደሩ አሳስበዋል።

የከልሉንም ይሁን የሀገሪቱን ሰላም ለማወክ በውጭና በሀገር ውሰጥ ያሉ አንዳንድ አካላት ሰፊ ወሬ እየነዙ መሆኑን የገለጹት ርእሰ መስተዳደሩ፥ በትናንትናው እለት በጎንደር የተከሰተው ይኸው ነው ብለዋል።

በትናንትናው እለት በማረሚያ ቤት የሚገኘውን ኮሌኔል ደመቀ ዘውዱን ወደ ሌላ ቦታ ሊወስዱት ነው በሚል በማህበራዊ ድረ ገጽ እና በጸረ ሰላም ሀይሎች በተነዛ ወሬ በከተማዋ ከፍተኛ ውጥረት ተፈጥሮ እንደነበር ተናግረዋል።

ግለሰቡ በወንጀል ተጠርጥሮ በህግ ቁጥጥር ስር የሚገኝ እንደመሆኑ መጠን ህግ በሚፈቅደው አግባብ እንደሚፈፀም ተናግረዋል።
ግለሰቡን ወደሌላ ቦታ ማዘዋወር ቢፈለግ ኖሮ በህግ ጥላ ስር ከዋለበት ቀን ጀምሮ መፈፀም ይቻል ነበር፣ ሆኖም ህብረተሰቡ ለሚያነሳቸው ጥያቄዎች አክብሮት በመስጠት በዚሁ ጉዳይ ላይ ከህዝቡ ጋር ለመወያየትና ለመግባባት መንግስት ወስኗል ብለዋል።

መንግስት ይህን ወስኖ እያለና ተጠርጣሪውን በተመለከት ምንም አይነት የተለየ እንቅስቃሴ በሌለበት ሁኔታ ጎንደርና አካባቢው እንዲተራመስ የሚፈልጉ ሃይሎች ውዥንብር በመፍጠራቸው ያለመረጋጋት ተከስቷል።

ህዝቡ ጉዳዩን በመረዳቱ የደረሰ ጥፋት ግን አለመኖሩን አስታውቀዋል።

ህብረሰተቡ ግጭችን ለማባባስ የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች ሴራ ተረድቶ ለሰላምና ለህግ የበላይነት በመትጋት መንግስት አካባቢውን ወደ መደበኛ ሁኔታ እንዲመለስለ ለማድረግ በሚያደርገው እንቅስቃሴ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

መንግስት ሁሉንም ችግሮች ከህብረተሰቡ ጋር በመሆን መፍታት እንደሚቀጥልም ነው ርዕሰ መስተዳደሩ አስገንዝበዋል።