Widgetized Section

Go to Admin » Appearance » Widgets » and move Gabfire Widget: Social into that MastheadOverlay zone

ወጣቱ ትውልድ ስሜት ቀስቃሽ የአሉባልታ መረጃዎችን በመመከት ልማቱን ከሚያደናቅፉ ተግባራት ሊቆጠብ ይገባል ተባለ

youth role

አዲስ አበባ ፣ ነሃሴ 25 ፣ 2008 (ኤፍ ቢ ሲ) ወጣቱ ትውልድ ስሜት ቀስቃሽ የሆኑ የአሉባልታ መረጃዎችን በምክንያታዊነት በመመከት ሀገሪቱ የጀመረችውን ልማት ከሚያደናቅፉ ተግባራት ሊቆጠብ እንደሚገባ የፌደራል እና አርብቶ አደር ጉዳዮች ሚኒስትር አቶ ካሳ ተክለብርሀን ተናገሩ።

የወጣቶች የነቃ ተሳትፎ እና ተጠቃሚነት ለህዳሴያችን በሚል መሪ ቃል አራተኛው ሀገር አቀፍ የወጣቶች ኮንፈረንስ ዛሬ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።

በዛሬው መርሃ ግብር ላይ ስኬታማ ወጣቶች ተሞክሯቸውን ያቀረቡ ሲሆን፥ ህብረ ብሄራዊ የፌደራል ስርዓት ግንባታ እና የኢትዮጵያ ህዳሴ የሚል ጽሁፍ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።

በጽሁፉ ህገ መንግስቱ የኢትዮጵያን ብሄር ብሄረሰቦች መብት እና እኩልነት ማስከበሩን እና የህዝቦችን ተጠቃሚነትና ተሳታፊነት ማረጋገጡን ያሳየ መሆኑ ተገልጿል።

ጠባብነት፣ ትምክህት እና መልካም አስተዳደር የስርዓቱ ተግዳሮቶች መሆናቸውም በውይይቱ ላይ ተነስቷል።

ይህን በመጠቀም የቀለም አብዮት ለማስነሳት የሚንቀሳቀሱ ሃይሎች መኖራቸውንም ሚኒስትሩ አቶ ካሳ ተናግረዋል።

ሚኒስትሩ በንግግራቸው ለህገ መንገስቱ ተገዥ መሆንና ከመንግስት ጎን በመሆን የተጀመሩ የልማት ስራዎችን ማስቀጠል ከወጣቱ እንደሚጠበቅም አንስተዋል።

መንግስት ችግሮችን ለምን ቶሎ አይፈታም በሚል የውይይቱ ተሳታፊ ወጣቶች ላነሱት ጥያቄ ምላሽ የሰጡት ሚኒስትሩ፥ የፍጥነት ችግር ካልሆነ በቀር ችግሮች እንደሚፈቱ አስረድተዋል።

ወጣቶች ጥያቄዎቻቸውን በሰላማዊ መንገድ እንጅ መሰረተ ልማቶችን በማፍረስ መሆን የለበትም ብለዋል።

የታሰበው ተሃድሶን ተፈጻሚነት በተመለከተም፥ መንግስት የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት በመወሰኑ የተባለውን ተሃድሶ ያደርጋልም ነው ያሉት አቶ ካሳ።

በሃገሪቱ ካለው ወቅታዊ ሁኔታ ጋር ተያይዞ በሰጡት ማብራሪያ፥ ህገ መንግስቱ በአዋሳኝ ክልሎች ለሚፈጠሩ ችግሮች የራሱ አሰራር እንዳለውም ገልጸዋል።

ከዚህ ባለፈ ግን ወጣቶች ጥያቄውን ተመርኩዘው የሚያማልል የሚመስል ስሜት ቀስቃሽ የትምክህትና የጠባብነት የአሉባልታ መረጃን የሚያስተላልፉ ሃይሎችን ከስሜት በፀዳ መልኩ ምክንያታዊ በመሆን መመከት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

ሚኒስትሩ ወጣቱ ትውልድ የተጀመረውን ልማት ከሚያደናቅፉ ተግባራት ሊቆጠቡ እንደሚገባም ነው የገለጹት።

በነገው እለትም ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ በኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ዙሪያ ወጣቶቹ ለሚያነሷቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ እንደሚሰጡ ይጠበቃል።