Widgetized Section

Go to Admin » Appearance » Widgets » and move Gabfire Widget: Social into that MastheadOverlay zone

የኦሮሚያ እና የአፋር ብሄራዊ ክልሎች ሰሞኑን በሰሜን ጎንደር የተፈጸመውን ድርጊት አወገዙ

Gonder act denounced
አዲስ አበባ ፣ ሃምሌ 11 ፣ 2008 (ኤፍ ቢ ሲ) የኦሮሚያ እና የአፋር ብሄራዊ ክልሎች ሰሞኑን በሰሜን ጎንደር ዞን በጸረ ሰላም ሀይሎች የተፈጸመውን ህገወጥ ድርጊት አውግዘዋል።

የሻዕቢያ መንግስት በአስመራ አሰልጥኖ ባሰማራቸው የጥፋት ቡድን አባላቱ አማካኝነት፥ ሰሞኑን በጎንደር በንፁሃን ዜጎችና በፀጥታ ሃይል አባላት ላይ በደረሰው የህይወትና የአካል ጉዳት የተሰማቸውን ጥልቅ ሃዘንም ክልሎቹ ገልጸዋል።

የሻዕቢያ እና የተላላኪዎቹ የሽብር ተልዕኮ በሕዝቦች የተባበረ ሃይል ይመክናል ያለው የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት መግለጫ፥ በሰሞኑ እንቅስቃሴውም ለዘመናት አብሮ የኖረውን ሕዝብ እርስ በእርሱ ለማጫረስ ያደረገው ጥረት በሕዝቦች አርቆ አስተዋይነት መገታቱን አንስቷል።

ሃገሪቱ እያስመዘገበች ያለው ሁለንተናዊ ለውጥ ያልተዋጠለት ሻዕቢያ፥ የሃገሪቱን ሰላም ለማደፍረስና የተጀመረውን የህዳሴ ጉዞ ለማደናቀፍ የማይፈነቅለው ድንጋይ አለመኖሩንም መግለጫው አመላክቷል።

ሻዕቢያ የሚያቀነባብራቸው የጥፋት ዘመቻዎች በሕዝቦችና በፀጥታ ሃይሉ የጋራ ጥረት እየተመታ ሲከሽፍ የቆየ ቢሆንም ይህ የሽብር ቡድን ዛሬም ከተለመደው የሽብር ድርጊቱ ሊታቀብ እንዳልቻለም መግለጫው አስታውሷል፡፡

ሰሞኑን በአስመራ አሰልጥኖ ባሰማራቸው የጥፋት ቡድን አባላቱ አማካኝነት በጎንደር በንፁሃን ዜጎችና በፀጥታ ሃይል አባላት ላይ የህይወትና የአካል ጉዳት ማድረሱም የዚሁ ማሳያ መሆኑን የክልሉ መንግስት አመልክቷል።

የአፋር ክልል ብሄራዊ ክልላዊ መንግስትም በሰሜን ጎንደር በጸረ ሰላም ሃይሎች በተፈጠረው ሁከት ሳቢያ፥ በንጹሃን ዜጎችና በጸጥታ ሃይል አባላት ላይ በደረሰው የህይወትና የአካል ጉዳት የተሰማውን ጥልቅ ሃዘን ገልጿል።

በዚህ ጸረ ሰላም ደርጊት የተሳተፉ ግለሰቦችና ቡድኖች ጉዳይም፥ በህግ ተጣርቶ ለፍርድ እንዲቀርቡም ነው ያሳሰበው።

የሽብር ድርጊቱን ሲከላከሉ አኩሪ መስዋዕትነት ለከፈሉ የፌደራልና የክልሉ ፖሊስ አባላትና የጥቃቱ ሰለባ ለሆኑ ንፁሃን ዜጎች የተሰማውን ልባዊ ሀዘን እየገለጸ ለቤተሰቦቻቸውና ለስራ ባልደረቦቻቸው መጽናናትን ተመኝቷል።