Widgetized Section

Go to Admin » Appearance » Widgets » and move Gabfire Widget: Social into that MastheadOverlay zone

የሕግ የበላይነትን የማስከበር ጉዳይ ለድርድር አይቀርብም:- ከንቲባ ድሪባ ኩማ

AA Addis ababa 12
ሐምሌ 1፣2008

ሕገወጥ የመሬት ወረራን የመከላከልና የህግ የበላይነትን የማስከበር ጉዳይ ለድርድር የማይቀርብ የህልውና ጉዳይ በመሆኑ እርምጃው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የአዲስ አበባ ከንቲባ አቶ ድሪባ ኩማ ገለፁ፡
የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት 3ኛ ዓመት የስራ ዘመን 3ኛ መደበኛ ጉባኤ በመካሄድ ላይ ነው፡፡

ከንቲባ አቶ ድሪባ ኩማ የከተማ አስተዳደሩን የ2008 በጀት አመት እቅድ አፈፃፀም ሪፖርትና የ2009 በጀት አመት የእቅድ አቅጣጫን ለምክር ቤቱ አቅርበዋል፡፡

ከንቲባው በሪፖርታቸው ሕገወጥ የመሬት ወረራን ለመግታትና የተወረረውንም መሬት ለማስመለስ የሚደረገውን ጥረት ለማደናቀፍ ኪራይ ሰብሳቢዎችና ሕገወጥ የመሬት ወራሪዎች ከፍተኛ ጥረት ቢያደርጉም ሕግ የማስከበር ስራው መቀጠሉንም ገልጸዋል፡፡

ለምክር ቤቱ በቀረበው ሪፖርት መሰረት ባለፈው በጀት አመት የከተማ አስተዳደሩ በመልካም አስተዳደር ዘርፍ ተጨባጭ ለውጥ ማምጣቱ ተገልጿል፡፡

ለአብነትም የህዝብ እርካታን በገለልተኛ ወገን በማስጠናት ህብረተሰቡ ባገኘው አገልግሎት እየረካ መምጣቱን ተመልክቷል፡፡

የመልካም አስተዳደር ችግር የፈጠሩ 346 አመራሮችና 2815 ፈፃሚዎች ላይ እንደየጥፋታቸው ተጠያቂ መደረጋቸውንም ከንቲባው አመልክተዋል፡፡

የስራ እድል ፈጠራን በተመለከተ በበጀት አመቱ ከ195 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል ተፈጥሯል ብለዋል፡፡

የቤት ልማትን በተመለከተ የ40/60 ነባር 1292 ቤቶች ግንባታ አፈጻጸም ከ96 በመቶ በላይ የተጠናቀቀ ሲሆን በቅርብ ቤቶቹን ለዜጎች ለማስተላለፍ ዝግጅት መጠናቀቁን ገልፀዋል፡፡

በማህበራዊ፣ በመሰረተ ልማት፣ ሕገወጥ ንግድ፣ በመሬት አስተዳደርና በቱሪዝም ዘርፍ የተከናወኑ ተግባራት ባለፈው በጀት ዓመት በአፈፃፀማቸው መሻሻል ማሳየታቸውን ከንቲባው አስረድተዋል፡፡

የመልካም አስተዳደር ችግሮችን መቅረፍ፣ አዲሱን የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ተግባራዊ ማድረግ፣ የስራ አጥነትን ትርጉም ባለው መልኩ መቅረፍና ልማታዊ የመሬት አስተዳደር መፍጠር የ2009 በጀት አመት የትኩረት አቅጣጫዎች ናቸው፡፡