Widgetized Section

Go to Admin » Appearance » Widgets » and move Gabfire Widget: Social into that MastheadOverlay zone

እስራኤል ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ከንጉስ ሰለሞን ጀምሮ የዘለቀውን ግንኙነቷን የበለጠ ታጠናክራለች- ጠ/ሚ ቤኒያሚን ኔታኒያሁ

natanyahu
እስራኤል ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ከንጉስ ሰለሞን ጀምሮ የዘለቀውን ግንኙነቷን የበለጠ ታጠናክራለች- ጠ/ሚ ቤኒያሚን ኔታኒያሁ.
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 30፣ 2008 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በኢትዮጵያ ይፋዊ የስራ ጉብኝት በማድረግ ላይ የሚገኙት የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታኒያሁ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው ንግግር አድርገዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያደረጉት ንግግር የተከፈተው በምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ አቶ አባዱላ ገመዳ ነው።

አፈ ጉባኤ አቶ አባዱላ ገመዳ ኢትዮጵያ ከእስራኤል ብዙ መቅሰም የምትፈልጋቸው ነገሮች አሉ ብለዋል።

በተለይም በግብርና ዘርፍ፣ በመስኖ ልማት እና የውሃ አጠቃቀምን ነው ያነሱት።

እንዲሁም ኢትዮጵያ ወደ መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገራት ተርታ ለመቀላቀል እና ወደ ኢንደስትሪ ለምታደርገው ሽግግር ከእስራኤል ጋር መስራት ትፈልጋለች ብለዋል።

በኢትዮጵያ እና በእስራኤል መካከል ያለው ግንኙነት እንዲጠናከር ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ለሰሩት ስራም ምስጋናም አቶ አባዱላ አቀርበዋል።፥ ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁን ለንግግር ጋብዘዋቸዋል።

የአፈ ጉባኤውን ግብዣ ተከትሎ ንግግር ያቀረቡት ጠቅላይ ሚንስትር ቤንያሚን ኔታኒያሁ በ30 ዓመታት ውስጥ ኢትዮጵያን ለመጀመሪያ ጊዜ የጎበኘ የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስተር በመሆኔ በጣም ደስታ ተሰምቶኛል በማለት የቀደሙ የአገራቸው መሪዎች ኢትዮጵያን ለዚህን ያህል ጊዜ ሳይጎበኙ መቆየታቸው ጥያቄ ፈጥሮብኛል ብለዋል።

የኢትዮጵያ እና የእስራኤል ህዝብ በጣም የተቀራረበ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ የኢትዮጵያውያን ልብ ውስጥ እስራኤል እንዳለች ሁሉ በእስራኤላውያን ልብ ውስጥም ኢትዮጵያ አለች ሲሉ ተናግረዋል።

በተለይም ቤተ እስራኤላውያን የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት እንዲዳብር ከፍተኛ ሚና እንደተጫወቱ በመጠቆም፥ ቤተ እስራኤላውያኑ እስራኤላዊ ነኝ በሚለው እንደሚኮሩ ሁሉ ኢትዮጵያዊ ነኝ በሚለውም በጣም ኩራት ይሰማቸዋል ነው ያሉት።

ኢትዮጵያ ባለ ትልቅ ታሪክ ባለቤት ነች ያሉት ኔታኒያሁ፥ ነፃነቷን ለማስጠበቅ ያደረገችውን ትግል እስራኤል ታደንቃለች፤ ሀገሪቱ ለነፃነት ያደረገችው ትግል ከእስራኤል ጋር ያመሳስላታል የሚለውንም በንግግራቸው አንስተዋል።

የኢትዮጵያ እና እስራኤል ከንጉስ ሰለሞን ጀምሮ እስከዛሬ በክርስትና የዘለቀ ግንኙነት አላቸው፤ ይህንን ግንኙነት በሁሉም ዘርፍ አጠናክረን እንቀጥላለን ሲሉም አብራርተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታኒያሁ፥ የሀይማኖት ነፃነት በሁሉም ሀገር ሊከበር ይገባል ያሉ ሲሆን፥ ኢትዮጵያ ለሁሉም ሀይማኖቶች እኩል እውቅና ሰጥታ የምታከብር በመሆና ከእስራኤል ጋር ያመሳስላታልም ነው ያሉት።

በአሁኑ ጊዜ ዘር፣ ሀይማኖት፣ ጾታ እና ዕድሜ ሳይለይ በሁሉም የዓለማችን ክፍሎች ላይ ጉዳት እያደረሰ ያለውን ሽብርተኝነት ለመከላከል ኢትዮጵያ የምታደርገውን ጥረት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አድንቀዋል።

ከኢትዮጵያ በፊት ጉብኝት ባደረጉባቸው ሶስት የአፍሪካ ሀገራት ሽብርተኝነትን መከላከል በሚቻልበት ዙሪያ መምከራቸውን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ይህን የዓለም ጠላት የሆነውን ሽብርተኝነት ለመዋጋት ሀገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር እንደምትሰራም አስታውቀዋል።

አሁን ጊዜው የአፍሪካ ነው፤ ፊታችንን ወደ አፍሪካ እናዞራለን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ፥ በተለይም ከአፍሪካ በሚያስገርም ፍጥነት በማደግ ላይ ካለችው ኢትዮጵያ ጋር ለመስራት ዝግጁ ነን ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ በከፍተኛ ፍጥነት በማድግ ላይ ያለች ሀገር መሆኗን ያነሱ ሲሆን፥ እስራኤል ከኢትዮጵያ ጋር ስትሰራ ኩራት እንደሚሰማት ተናግረዋል።

ሁለቱ ሀገራት በጋራ ለመስራት ስምምነት ላይ ከደረሱባቸው በሳይንስና ቴክኖሎጂ እንዲሁም በባሕልና ቱሪዝም መስኮች በተጨማሪም በሌሎች መስኮችም ሀገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ለመስራት ዝግጁ መሆኗን ጠቅሰዋል።

በተለይም በትምህርት፣ በግብርና እና የእንሰሳት ሀብት ልማት እስራኤል ከኢትዮጵያ ጋር ለመስራት ፍላጎት አላት ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ ለምክር ቤቱ ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ የጋራ ስምምነታችንን በተግባር እንደግመዋለን ሲሉም አረጋግጠዋል።

“በአሁኑ የኢትዮጵያ ጉብኝቴ በጣም ደስተኛ ነኝ፤ ባለቤቴን ጨምሮ ከኔ ጋር ወደ ኢትዮጵያ የመጡት በሙሉ ደስተኞች ናቸው፤ ኢትዮጵያን በድጋሚ እንደምጎበኝ እርግጠኛ ነኝ” በማለትም ተናግረዋል።