Widgetized Section

Go to Admin » Appearance » Widgets » and move Gabfire Widget: Social into that MastheadOverlay zone

ኢትዮጵያ ወደ ደቡብ ሱዳን ተጨማሪ ሰላም አስከባሪዎችን ለመላክ ዝግጁ መሆኗን ገለፀች

ethio to send troops
አዲስ አበባ፣ ሃምሌ 9፣ 2008 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ኢትዮጵያ የደቡብ ሱዳንን ሰላም እና መረጋጋት ለማረጋገጥ ተጨማሪ ሰላም አስከባሪዎችን ለመላክ ዝግጁ መሆኗን አስታወቀች።

የደቡብ ሱዳን የሰላም ስምምነት ተፈፃሚ እንዲሆን ሀገሪቱ አሁንም ከኢጋድ ጋር በመሆን ድጋፏን እንደምትቀጥልም ነው የገለፀችው።

የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ፅህፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር አቶ ጌታቸው ረዳ ትናንት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የደቡብ ሱዳን ሰላም ማስከበር ተልዕኮን ለማገዝ ዝግጁ ናት ብለዋል።

የሀገሪቱን ሰላም ለመመለስ ኢትዮጵያ እንደከዚህ ቀደሙ አሁንም አጋርነቷን ታሳያለችም ብለዋል ኃላፊ ሚኒስትሩ።

ደቡብ ሱዳናውያን ልዩነታቸውን እንደሚያረግቡ ተስፋ አድርጋለሁ ያሉት አቶ ጌታቸው፥ ይህ ካልሆነ ግን ተጨማሪ ሰላም አስከባሪዎችን ለመላክ ዝግጁ ነን ብለዋል።

ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የደቡብ ሱዳን ተልዕኮ ውስጥ ከፍተኛ ቁጥር ያለውን ሰላም አስከባሪ ያሰማራች ሀገር መሆኗ ይታወቃል።

በሀገሪቱ በአጠቃላይ ከተሰማሩት ሰላም አስከባሪዎች (ፖሊስን ጨምሮ) 13 ሺህ 500 የሰው ሀይል ውስጥ 8 ሺህ 300 ያህሉ ኢትዮጵያውያን ናቸው።

ባለፈው ሳምንት በደቡብ ሱዳን መዲና ጁባ የፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር ታማኝ ሀይሎች እና የሪክ ማቻር ደጋፊዎች በቀሰቀሱት ከባድ ግጭት ከ300 በላይ ሰዎች መሞታቸው ይታወሳል።

መሪዎቹ ምንም እንኳን የሰላም ስምምነት ቢፈራረሙም ለሀገራቸው ህዝብ የገቡትን ቃል አፍርሰዋል ነው ያሉት አቶ ጌታቸው።

በመሆኑም መንግስት በደቡብ ሱዳን ሰላም እና መረጋጋት ለማስፈን የበኩሉን ድርሻ መወጣቱን እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

በሌላ በኩል በሀረሬ ተልዕኮ በዚምባብዌ፣ ዛምቢያ እና ማላዊ ተሰማርተው የነበሩ 200 ኢትዮጵያውያን ሰላም አስከባሪዎችን ወደ ሀገራቸው የመመለሱ ስራ መጀመሩን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።

ባለፈው ሳምንትም 17 ኢትዮጵያውያን ከማላዊ መመለሳቸው ተገልጿል።