Widgetized Section

Go to Admin » Appearance » Widgets » and move Gabfire Widget: Social into that MastheadOverlay zone

ግንቦት 20 ሀገሪቱን ወደ ነበረችበት ከፍታ ለመመለስ የሚያስችል አቅጣጫ የተያዘበት ታሪካዊ ቀን ነው

ግንቦት 20 ሀገሪቱን ወደ ነበረችበት ከፍታ ለመመለስ የሚያስችል አቅጣጫ የተያዘበት ታሪካዊ ቀን ነው
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 17፣ 2008 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ግንቦት 20 የኢትዮጵያ ህዝቦችን ከአስጨናቂው ጭቆና ከማላቀቁም ባለፈ ሀገሪቱን ወደ ነበረችበት ከፍታ ለመመለስ የሚያስችል ትክክለኛ አቅጣጫ የተያዘበት ታሪካዊ ቀን ነው አሉ የኢህአዴግ ሊቀመንበርና የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ፡፡

የኢትዮጵያን ህልውና በፅኑ የፈተነውንን አስከፊውን ድህነት ለመለወጥ በተደረገው ሰፊ ጥረትም የሀገሪቱ ዜጎች በሁሉም ዘርፍ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግ እየተቻለ መሆኑን አንስተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የግንቦት 20ን 25ኛ አመት የብር ኢዩቤልዩ በዓልን አስመልክተው ከጋዜጠኞች ጋር ባደረጉት ቆይታ፥ ግንቦት 20 ለኢትዮጵያ መሰረታዊ የስርአት ለውጥ ያመጣ ቀን ነው ብለዋል።

ይህ ውጤታማ ለውጥ እጅግ መራራ ትግል እና ከፍተኛ መስዋዕትነት ተከፍሎበት የተገኘ መሆኑን ጠቅሰው፥ ከ25 አመት በፊት ግንቦት 20 1983 ጀምሮ መሰረታዊ ለውጡ ሲጀመር ሶስት አበይት ጉዳዮች ትኩረት ተሰጥቷቸው እንደነበረም ተናግረዋል።

የመጀመሪያው ሀገሪቱ የነፃ ገበያ ስርአት መከተል መጀመሯ እና የዜጎችን እኩል ተጠቃሚነትን ማረጋገጧ ነው።

ብዝሃነትን የሚያስተናግድ የመድብለ ፓርቲ ዴሞክራሲያዊ ስርአት መገንባት መጀመሯም የመሰረታዊ ለውጡ አንኳር ጉዳይ ነው።

ሶስተኛው ደግሞ አሃዳዊውን ስርአት የጣለው መንግስት የብሄር ብሄረሰቦችን መብት የሚያስተናግድ መንግስታዊ መዋቅር እንዲመጣ ያደረገው ለውጥ ነው ሲሉ ጠቅሰዋል።

መሰረታዊው የስርአት ለውጥ ከሚገለፅባቸው ነገሮች አንዱ የትምህርት ዘርፍ ነው ያሉት አቶ ኃይለማርያም፥ ከሀገሪቱ ህዝብ ወደ 27 ሚሊየን የሚሆኑት በትምህርት ገበታ ላይ እንደሚገኙም ጠቁመዋል።

በዚህ ስርአት ውስጥ ተወዳድሮ ለማሸነፍ ለሚያስፈልገው እውቀት እና ክህሎት ወይንም የሰው ሀብት ልማቱ የተለየ ትኩረት ተሰጥቶቷልም ነው ያሉት።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለፉት አመታት መንግስት እና ህዝቡ ባደረጉት ሰፊ ርብርብ ኢትዮጵያን ከኋላቀርነቷ የሚያላቅቃት የሰው ሀብት ክምችት መፈጠሩንም አመላክተዋል።

የግብርናው ዘርፍ በየደረጃው እየጎለበተ መጥቷል፤ ለገበያ የሚያቀርብ አርሶ አደር በስፋት እየተፈጠረ መምጣቱም ለነፃ ገበያ ስርአቱ ግንባታ ወሳኝ ነው የሚለውንም አንስተዋል።

በቀጣይም ከግብርናው ወደ አምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ የሚደረገውን ሽግግር ለማቀላጠፍ ሰፊ ስራዎች ይጠብቁናል ነው ያሉት።

አሁን የሚታየውን ለውጥና ተስፋ በጽኑ መሰረት ላይ ለማቆምም የብልሽ አሰራሮችና የኪራይ ሰብሳቢነትን መሰናክሎች ማስወገድ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ትኩረት የሚሻ ጉዳይ ነው ብለዋል።

ከዚህ ባለፈም ድህነትን ሙሉ ለሙሉ ማስወገድና የዜጎችን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ እንዲሁም በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ መሰረተ ልማትን በማሟላት ብልሹ አሰራርን ማስወገድ፥ ዋነኞቹ የትኩረት አቅጣጫዎች መሆናቸውን አስረድተዋል።

በአጠቃላይ ግንቦት 20 ከጨለማ ወደ ብርሃን የተሸጋገርንበት እና የሀገሪቱ ህልውና ተረጋግጦ የህዳሴው ጉዞ የተጀመረበት ቀን ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ እንኳን ለግንቦት 20 25ኛ አመት የብር ኢዩቤልዩ በአል አደረሳችሁ በማለት መልካም ምኞታቸውን አስተላልፈዋል።