Widgetized Section

Go to Admin » Appearance » Widgets » and move Gabfire Widget: Social into that MastheadOverlay zone

ያለፉት 25 ዓመታት የኢትዮጵያን መፃኢ ተስፋ አለምልመዋል – ዶ/ር ደብረፅዮን

ያለፉት 25 ዓመታት የኢትዮጵያን መፃኢ ተስፋ አለምልመዋል ዶር ደብረፅዮን
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 16፣ 2008 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በብዙ ችግሮች የተፈተነው ያለፉት 25 ዓመታት ኢኮኖሚያዊ እድገት የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ገፅታ የቀየረ ነው አሉ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የፋይናንስና ኢኮኖሚ ክላስተር አስተባባሪ እና የመገናኛና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል።

ዶክተር ደብረፅዮን ከጣቢያችን ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደ ገለፁት የተመዘገበው ኢኮኖሚያዊ እድገት ሃገሪቱ ባጋጠማት ከባድ ድርቅ ተፈትኖም ውጤታማነቱን አሳይቷል።

ሚኒስትሩ እንደሚሉት፥ ኢትዮጵያ ዘንድሮ ያጋጠማት ድርቅ በ1977 ካጋጠማት የባሰ እና በ50 ዓመት ታሪክ ውስጥ ታይቶ የማይታወቅ ነው።

የሃገሪቱ እድገት ሳይገታ ድርቁን ለመቋቋም እንዲቻል ታስቦ የለጋስ ሃገራት ድጋፍ ቢጠየቅም በሚፈለገው ልክ ሊገኝ አልቻለም።

ባለፉት 25 ዓመታት አገሪቱ የፈጠረችው ኢኮኖሚያዊ አቅም ግን በራሷ አቅም እና በጥቂት የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ድጋፍ ያለምንም ኮሽታና ጫጫታ ይህን ከባድ የተባለ ድርቅን ልትቋቋም ችላለች።

ይህም የሃገሪቱ ኢኮኖሚ ከመሰረቱ ጥንካሬን እየያዘ ለመምጣቱ ማሳያ መሆኑን ያነሳሉ።

ዶክተር ደብረፅዮን ዛሬ እንደ ድሮ አይደለም፤ ያለፉት ሁለት አስርት ዓመታት አድገት ሰፊውንና ብዙሃኑን ኢትዮጵያዊ ተጠቃሚ ያደረገም ሆኗል።

የመንግስት ዋነኛ ተግባር ሁሉም ዜጋ ለሃብት የሚሮጥበትን ምቹ መደላድል መፍጠር መሆኑን ዶክተር ደብረፅዮን ያነሳሉ።
Aid

ይህን የሚያሳኩ ከትምህርት እስከ ጤናው ዘርፍ፣ ከመንገድ አውታር ዝርጋታ እስከ መብራት እና ውሃ መሰረተ ልማት ድረስ እስከ ውስኑነቶችም ቢሆን ከገጠር እስከ ከተማ በፍትሃዊነት ተደራሽ እንዲሆኑ ጥረት በመደረጉ ኢኮኖሚያዊ እድገት እውን ሆኗል ባይ ናቸው።

ዛሬ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከአስር ፈጣን አዳጊ ሃገራት አንዱና ቀዳሚው ተደርጎ በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እውቅና የሚቸረው ሆኗል የሚሉት ዶክተር ደብረፅዮን፥ አሁን የቀደመ የከፋ ስሟም ተቀይሮ ዛሬ በአለም አደባባይ መልካም ገፅታን እየገነባች መጥታለች ብለዋል።

ይህም በመሆኑ ዛሬ በዓለም ዙሪያ ያሉ ትልልቅ ባለሃብቶችና ኩባንያዎች አይናቸውን የሚጥሉበት ኢኮኖሚ መሆኑን አንስተዋል።

እነዚህ ባለሃብቶች ወደዚህች ሃገር መዋዕለ ንዋያቸውን ለማፍሰስ ሲመጡ እያደገ ካለው የሃገሪቱ ኢኮኖሚም ለመጠቀም ሲሉም ነው።

ይህ ከምንም በላይ ኢትዮጵያ መፃኢ ተስፋዋ የለመለመ መሆኑን ያሳያል ባይ ናቸው።

ያለፉት ዓመታት እድገት ያመጣው ማህበረሰባዊ ለውጥ የህዝቡን የመልማት ፍላጎት ማነሳሳቱን ዶክተር ደብረፅዮን ተናግረዋል።

እንግዲህ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊ እድገት በሁለት አሃዝ እየተመነደገ የሃገሪቱ ገፅታ መቀየር የጀመረው ከ1994 ወዲህ ነው።

ኢህአዴግ የደርግን ስርዓት ገርስሶ ወደ ስልጣን ከመጣ ከ1983 እስከ 1994 ድረስ የነበሩት ዓመታት ኢኮኖሚያዊ እድገቱ የሚያረካ አልነበረም።

ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ አንድም ከኤርትራ ጋር የተፈጠረው ጦርነት ኢኮኖሚው ያመነጫው ሃብት ለጦርነት እንዲገበር በማድረጉ መሆኑን ሚኒስትሩ ያነሳሉ።

እንደእሳቸው ትክክለኛና ወጥ የሆነ ልማታዊ ፖሊሲዎች እና ስትራቴጂዎች ወደ ተግባር ያለመግባታቸውም ሌላው ምክንያት ነው።

ታዲያ ኢኮኖሚያዊ እድገቱ ከ1994 አስቀድሞ ተጀምሮ ቢሆን ኖሮ ዛሬ በርካታ ለውጦች በዚች ሃገር በተፈጠሩ ነበር ሲሉ ይቆጫሉ።

እንዲያም ሆኖ ግን በፈተናም ታጅቦ በሃገሪቱ የተመዘገበው ኢኮኖሚያዊ እድገት በአጭር ዓመታት የተገኘ እንደመሆኑ በሚፈለገው ልክ አይሁን እንጂ እንደ አጠቃላይ በጎ የሚባል ነው ይላሉ።

እንዲህ እየተመነደገ ያለ ኢኮኖሚ ከፊቱ ፈተናዎች ተጋርጠውበታል ።

የኪራይ ሰብሳቢነት አስተሳሰብና ከእሱ ጋር ተያይዞ የመልካም አስተዳደር እጦት ትልቁ ጋሬጣ ሆነዋል የሚሉት ዶክተር ደብረፅዮን፥ እዚህ ላይ ማህበረሰቡ ውስጥም “ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል” የሚለው የተሳሳተ አስተሳሰብ መኖሩም ጥቅመኝነት እንዲነግስ አስተዋፅኦ እያበረከተ ነው ብለው ያምናሉ።

ስለዚህ ለሃገሪቱ እድገት ማነቆ ነውና ይህ አስተሳሰብ መቀየር አለበት፤ ይህ ሲሆን የመልካም አስተዳደር እጥረቶችም እየተፈቱ ይሄዳሉ ብለዋል።

ሌላው ትልቁ ፈተና ነው ብለው ያስቀመጡት ኢኮኖሚው በሚፈለገው ልክ የማስፈፀም አቅም አለማደጉ ነው።

ለኪራይ ስብሳቢነትና ለመልካም አስተዳደር ችግሮች መንስኤውም የማስፈፀም አቅም ማጣት መሆኑን የሚያነሱት ሚኒስትሩ፥ በእርግጥ ይህን ለማረም የመንግስት ሰራተኛው በሰራው ልክ የሚመዘንበት ስርዓት መዘርጋቱን ገልፀዋል።

አሁን ደግሞ ይህን ስርዓት በፖለቲከኛ ሹመኛው ላይም በመተግበር የሚመራውን ተቋም ግብ በምን ያህል ግብ አሳክቷል አላሳካም የሚል የመመዘኛ ስርዓት የመዘርጋት ሃሳቦችና ጅምሮች መኖራቸውን ይጠቅሳሉ።

በዚህ መልኩም መንግስት የተያያዘውን የፈጣን እድገት ግቡን ለማስቀጠል በዋነኝነት ከፍተኛ አመራሩ ላይ ትኩረት አድርጎ እንደሚሰራ ነው ዶክተር ደብረፅዮን የተናገሩት።