Widgetized Section

Go to Admin » Appearance » Widgets » and move Gabfire Widget: Social into that MastheadOverlay zone

ወጣቶች ለዘላቂ ልማት የተጫወቱት ሚና ከፍተኛ ነው- አቶ በከር ሻሌ

beker shale
አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 14 ፣ 2008 (ኤፍ.ቢ.ሲ) አስተማማኝ ሰላም እንዲሰፍንና ቀጣይነት ያለው ዘላቂ ልማት በሀገሪቱ እንዲረጋገጥ ወጣቶች ባለፉት ዓመታት የተጫወቱት ሚና ከፍተኛ መሆኑን የኦሮሞ ህዝብ ዴክራሲያዊ ድርጅት (የኦህዴድ ) ማዕከላዊ ኮሚቴ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ በከር ሻሌ ገለጹ።

የኦህዴድ ወጣቶች ሊግ ሶስተኛ መደበኛ ጉባኤ “በወጣቶች የላቀ ተሳትፎ የአገራችን ህዳሴ ይረጋገጣል” በሚል መሪ ሀሳብ ትናንት በአዳማ ከተማ አባገዳ አደራሽ ተጀምሯል።

“የአገሪቱ ህዝቦች ከጭቆናና የአፈና አገዛዝ ለማላቀቅ ወጣቶች የከፈሉት የህይወት መሰዋእትነት ዛሬ ለተገኘው ዲሞክራሲያዊ ነፃነት መሰረት ነው” ሲሉ የኦህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ በከር ሻሌ በጉባኤው መክፈቻ ስነስርዓት ላይ ገልጸዋል፡፡

አቶ በከር ሻሌ እንዳመለከቱት የኦሮሞ ህዝብ እንዳይማር በማድረግ በድንቁርና በኋላቀርነት ተሸብቦ እንዲኖር የአፈና መዋቅር ዘርግቶ እየገዛ የነበረው ስርዓት ግብዓተ መሬቱ እንዲፋጠን ወጣቶች ታሪክ የማይረሳው ተጋድሎ ፈጽመዋል፡፡

የኦሮሞ ህዝብ የራሱን ዕድል በራስ የመወሰንና የማስተዳደር ህገ መንግስታዊ ዋስትና የሰጠ ስርዓት እንዲዲገነባ የኦሮሞ ወጣቶች ከሌሎች የዴሞክራሲ ሃይሎች ጋር በመሆን ህዝቡን ለድል ማብቃታቸውን ተናግረዋል፡፡

የህዝቦች እኩልነትና የነፃነት መሰረት የሆነው ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ወደ አዲስ ምዕራፍ ማሸጋገር ከአሁኑ ትውልድ የሚጠበቅ ሃላፊነት እንደሆነም ጠቁመዋል ።

የኦህዴድና የኢህአዴግ ወጣቶች ሊግ ሊቀመንበር ወጣት ሀሰን ዑሳ ” በበኩሉ ክልሉም ሆነ አገሪቷ አሁን የደረሱበትን ፈጣን ዕድገት ለማስቀጠል በድህነትና ኋላቀርነት ላይ መረባረብ አለብን “ብሏል።

ባለፉት ዓመታት የተገኘው አስተማማኝ ሰላም፣ልማትና ዴሞክራሲ በጠባቦች፣ በትምክህተኞችና ሃይማኖትን ሽፋን ባደረጉ ቡድኖች እንዳይቀለበስ ወጣቱ ተቀናጅቶ መንቀሳቀስ እንደሚገባውም አስገንዝቧል፡፡

የስርዓቱን መሰረት የሚሸረሽሩ የኪራይ ሰብሳቢነት አስተሳሰብና ድርጊት ወጣቱ በአፅንኦት ሊታገለው እንደሚገባም ወጣት ሀሰን ጠቁሟል፡፡

የኦህዴድ ወጣቶች ሊግ ሶስተኛ መደበኛ ጉባኤ በግንቦት 20 ድል 25ኛ ዓመት የብር ኢዮቤልዩ ክብረ በዓል ዋዜማ መካሄዱ ወጣቶች በሁሉም መስኮች ተሳትፏቸውንና ተጠቃሚነታቸውን በዘላቂነት ለማረጋገጥ ዳግም ቃላቸውን የሚያድሱበት መሆኑንም ተመልክቷል፡፡

ጉባኤው በሶስት ቀናት ቆይታው የሊጉን የስራ አስፈፃሚዎችና የኦዲት ኮሚቴዎችን መምረጥ ጨምሮ የተለያዩ አጀንዳዎች ላይ እንደሚመክር ለጉባኤው ከወጣው መረሃ ግብር ማወቅ ተችሏል።