Widgetized Section

Go to Admin » Appearance » Widgets » and move Gabfire Widget: Social into that MastheadOverlay zone

በትግራይ ክልል በ86 ሚሊየን ብር ወጪ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ግንባታዎች እየተካሄዱ ነው

tigray shcool
አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 12 ፣ 2008 (ኤፍ ቢ ሲ) ባለፉት አመታት በተሰሩ ስራዎች በትግራይ ክልል የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ሽፋን ማደጉን የክልሉ ትምህርት ቢሮ ገለጸ።

በክልሉ ሰሜን ምዕራብ፣ ማዕከላዊና ደቡብ ምስራቅ ዞኖች፥ ያለውን የአንደኛ ደረጃ የትምህርት ሽፋን የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ባልደረባ ተዘዋውሮ ጎብኝቷል።

የቢሮው ምክትል ሃላፊ አቶ ባታ ወልደሚካኤል እንዳሉት፥ መንግስት ባለፉት አመታት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ሽፋንን ለማሳደግ በርካታ ስራዎችን ሰርቷል።

በዚህም እድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ህጻናት በሙሉ የመማር እድል ማግኘታቸውን ተናግረዋል።

የ2ኛ ደረጃ የትምህርት ሽፋንን ለማሳደግም የአምስት አመት እቅድ ነድፎ እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው፥ በ86 ሚሊየን ብር ወጭ የትምህርት ቤት ግንባታዎች እየተካሄዱ ነው ብለዋል።

አሁን ላይም ለአምስት 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች አንድ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፥ እንዲሁም ለአምስት 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ደግሞ አንድ መሰናዶ ትምህርት ቤት የመገንባት ስራ እየተካሄደ መሆኑን አስረድተዋል።

በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሚታየውን የመምህራን እጥረት ለመቅረፍም፥ በሁሉም ፈረቃዎች መምህራን እየሰለጠኑ መሆኑን አንስተዋል።

በቀጣይም የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ሽፋኑን በማሳደግ አሁን ያለውን የ8 ኪሎ ሜትር ሽፋን ወደ 3 ለማድረግ እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።

የአካባቢዎቹ ነዋሪዎች በበኩላቸው ከዚህ ቀደም የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ሽፋን አለመዳረሱን ጠቅሰው፥ ባለፉት ሁለት አስርት አመታት ሁኔታው መቀየሩን ጠቁመዋል።

አሁን ላይም ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት በመላክ ማስተማር መቻላቸውን አውስተው፥ በአሁኑ ወቅት ቢያንስ በቀበሌ ደረጃ አንድ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መኖሩን ጠቅሰዋል።