Widgetized Section

Go to Admin » Appearance » Widgets » and move Gabfire Widget: Social into that MastheadOverlay zone

የፌዴራል ፖሊስና የማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን ተጠሪነት ተቀየረ

federal police comm
አዲስ አበባ ፣ሚያዝያ 07/2008(ዋኢማ)-ለፌዴራልና አርብቶ አደር ልማት ጉዳዮች ሚኒስቴር ተጠሪ የነበሩት የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽንና የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን መስሪያ ቤቶች ተጠሪነት በአዋጅ ተቀየረ፡፡

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አዋጆቹን ትናንት ሲያፀድቅ እንደተገለፀው የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ሆኗል፡፡ ይህም ኮሚሽኑ ኃላፊነቱን በተሻለ መልኩ እንዲወጣና በጥሩ ግንኙነት የህግ የበላይነትን ለማስከበር እንደሚያግዝ ተመልክቷል፡፡

ኮሚሽኑ በአገር ደህንነት፣በወንጀል መከላከል፣ወንጀል ተፈፅሞ ሲገኝ የወንጀል ምርመራ በማድረግ ተጠርጣሪን በማስረጃ መለየትና እና ሌሎች በርካታ አገራዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ኃላፊነት ያለበት ተቋም መሆኑ ተገልጿል፡፡ በመሆኑም ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ መሆኑ ተገቢና በሥራ ስምሪት ላይም ትልቅ ድርሻ ይኖረዋል ተብሏል፡፡

የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን ተጠሪነትም ለፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ እንዲሆን ተወስኗል፡፡ ይህም ኮሚሽኑ ከጠቅላይ ዐቃቤ ህጉ ጋር ተግባራዊ የሥራ ግንኙነት እንዲኖር ከማድረጉም በላይ የተሻለ ድጋፍና ክትትል ለማግኘትም ይረዳል ነው የተባለው፡፡

በምክር ቤቱ እንደተገለፀው የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን የወንጀል ቅጣት ውሳኔ የማስፈፀምና የማረም ተግባርን ያከናውናል፡፡ ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ በበኩሉ የቅጣት አፈፃፀምን የመከታተልና የታራሚዎችን አያያዝ የመከታተል ኃላፊነት አለበት፡፡ ስለሆነም የኮሚሽኑ ተጠሪነት ለጠቅላይ ዐቃቤ ህግ መሆኑ ተገቢና ጥብቅ የሥራ ትስስርና ግንኙነት እንዲፈጠር ያግዛል፡፡

በምክር ቤቱ የህግ፣ፍትህና አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት እና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በማሻሻያ ረቂቅ አዋጆቹ ላይ ጥያቄና አስተያየት እንዲያቀርቡ ማድረጉ በምክር ቤቱ ተመልክቷል፡፡ በቀረቡት ጥያቄዎችና አስተያየቶ ላይም የሚመለከታቸው አካላት ምላሽና ማብራሪያ እንዲሰጡ ተደርጓል፡፡