Widgetized Section

Go to Admin » Appearance » Widgets » and move Gabfire Widget: Social into that MastheadOverlay zone

በዘውዲቱ ሆስፒታል እንቅርት ለማውጣት ሆድ የቀደዱት ሐኪም ከሥራና ከደመወዝ ታገዱ

zeditu hospital
አንገት ላይ በማበጥ የሚታወቀውን እንቅርት (የአንገት ዕጢ) በቀዶ ጥገና ለማስወጣት ከወራት በፊት ተመዝግባ ስትጠባበቅ ከርማ ሚያዝያ 12 ቀን 2008 ዓ.ም. በቀጠሮዋ ቀን በዘውዲቱ መታሰቢያ ሆስፒታል የተገኘችውን ወጣት፣ አንገቷን ሳይሆን ሆዷን በመክፈት መልሰው የሰፉ ሐኪም ከሥራና ከደመወዛቸው መታገዳቸውን ሆስፒታሉ ለሪፖርተር ገለጸ፡፡

ሐኪሙ ልምድ ያላቸውና ለረዥም ጊዜ የሠሩ ቢሆኑም በተፈጸመው ስህተት የመጀመርያው ተጠያቂ በመሆናቸው የመጀመርያውን የዕግድ ዕርምጃ ሆስፒታሉ መውሰዱን፣ የዘውዲቱ ሆስፒታል ዋና ሥራ አስኪያጅ ዶ/ር ተረፈ አሰፋ ተናግረዋል፡፡

ለወራት ተራ በመጠበቅ ሚያዝያ 12 ቀን 2008 ዓ.ም. በወጣትነቷ አንገቷ ላይ አብጦ የሚታየውን እንቅርት በቀዶ ሕክምና ለማስወገድ ወደ ሆስፒታሉ ያመራችው የ23 ዓመቷ ወጣት ሰላም ደሞዜ ትባላለች፡፡ የሆስፒታሉ ዋና ሥራ አስኪያጅ ዶ/ር ተረፈ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ እንደ አጋጣሚና እንደ ዕድል ሆኖ በዕለቱ ቀዶ ሕክምና የሚደረግላት ሞክሼ ስም ያላት ሰላም ኪሮስ የምትባል ሌላ ታካሚ ነበረች፡፡

ሆስፒታሉ የመማር ማስተማር ሥራም ስለሚካሄድበት ቀድማ ወደ ቀዶ ጥገና ክፍል መግባት የነበረባት ሰላም ኪሮስ የነበረች ቢሆንም፣ ቀዶ ጥገና የሚደረግላቸውን ሕሙማን ቀደምት የሕክምና ታሪክ (Medical History) የሚመዘግቡ ተማሪዎች ሊያነጋግሯት ወደ ሌላ ክፍል ወስደዋት መዘግየቷን ገልጸዋል፡፡

ቀዶ ሕክምናውን ለመጀመር ሁሉም ነገር ተዘጋጅቶ የሚጠበቁት ሐኪሙ ስለነበሩ፣ ተራዋ የደረሰውና የሐሞት ከረጢት ቀዶ ጥገና የሚደረግላት ሰላም ኪሮስ የነበረች ቢሆንም፣ ሐኪሙ እንደመጡ ታማሚዋ እንድትገባ ሲጠይቁ የገባችው እንቅርት ለማስወጣት ተራዋን ስትጠባበቅ የነበረችው ሰላም ደሞዜ መሆኗን ሥራ አስኪያጁ ተናግረዋል፡፡

‹‹ሰላም›› የሚለውን ስም ብቻ በማየት ሁለት ነርሶችና አንድ የማደንዘዣ (ሰመመን) ባለሙያ ይዘው የገቡት ሐኪም፣ ማደንዘዣ ተወግታ በሰመመን ውስጥ የነበረችውን የእንቅርት ሕክምና ፈላጊዋን ሰላም ደሞዜ ሆድ መክፈታቸውንም ሥራ አስኪያጁ ጠቁመዋል፡፡

የሰላም ደሞዜ ሆድ እንደተከፈተ የሐኪሙ ረዳቶች የሕክምና ታሪክ መመዝገቢያውን ሰነድ ሲመለከቱ ሐኪሙ ያደረጉት ቀዶ ሕክምና ስህተት መሆኑን በማወቃቸውና በመናገራቸው፣ ሐኪሙ የሰላም ደሞዜን ሆድ ዘግተው አንገቷን በመክፈት እንቅርቷን እንዳወጡ ዶ/ር ተረፈ አስረድተዋል፡፡

በወቅቱ በተለይ የሰላም ደሞዜ ቤተሰቦች ከፍተኛ ድንጋጤና አለመረጋጋት ውስጥ ገብተው እንደነበር የገለጹት ሥራ አስኪያጁ፣ የሕክምና ባለሙያዎች እነሱን ካረጋጉ በኋላ ቀዶ ጥገናውን ያደርጉት ሐኪምና ሆስፒታሉ ታካሚዋንና ቤተሰቦቿን ይቅርታ መጠየቃቸውን ገልጸዋል፡፡

በወቅቱ ስህተቱ የተፈጸመው በሥራው ላይ በነበሩት ሐኪሙ፣ ነርሶቹና የማደንዘዣ ባለሙያው ቢሆንም፣ ዋናው ተጠያቂ ሐኪሙ በመሆናቸው ከሥራና ከደመወዝ በማገድ ለሕክምና ዲሲፕሊን ኮሚቴና ለሚመለከታቸው ሁሉ በማሳወቅ ውሳኔ እየተጠባበቁ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ከ1,200 በላይ ሕሙማን ተመዝግበው ለበርካታ ወራት ወረፋ በመጠበቅ ላይ በመሆናቸው፣ ካለፉት 15 ቀናት ጀምሮ በዘመቻ ሥራ ሕክምና በመስጠት ላይ መሆናቸውን የሚናገሩት ሥራ አስኪያጁ፣ ሰላም ደሞዜም ተራ ደርሷት የመጣች ታካሚ መሆኗን ተናግረዋል፡፡

ሐኪሙ የሆስፒታሉ ቋሚ ሠራተኛ ሳይሆኑ ባለው የሐኪም ችግር ምክንያት በኮንትራት ተቀጥረው እየሠሩ ያሉ የረጅም ዓመታት ልምድ ያላቸው መሆኑን የገለጹት ሥራ አስኪያጁ፣ በሆስፒታሉም ሆነ እሳቸው በሠሩበት ዘመን እንደዚህ ያለ ስህተት ተፈጽሞ እንደማያውቅ አስረድተዋል፡፡

አንድ ሐኪም የሕሙማኑን በሽታ ሳያውቅ፣ ማንነቱን ሳያረጋግጥና እምኑ ላይ ቀዶ ሕክምና እንደሚደረግለት ‘ሜዲካል ግራፍ’ ሳይኖረው የተኛን ሰው ዝም ብሎ እንዴት በቀዶ ሕክምና ሊከፍትና ሊዘጋ እንደሚችል የተጠየቁት ሥራ አስኪያጁ፣ ‹‹በዓለም አቀፍ ሕግ የሚታወቅ፣ የዓለም ጤና ድርጅትና ኢትዮጵያም የሚሠሩበት ‹ሜዲካል ቼክ ሊስት› የሚባል አሠራር እንዳለ ተናግረዋል፡፡

‹‹እንኳን ቀዶ ሕክምና ቀርቶ አንድ መድኃኒት ለታካሚ ሲታዘዝ አለርጂክ እንዳይሆንበት ደሙ ተረጋግጦ ነው የሚሰጠው፤›› ብለዋል ሥራ አስኪያጁ፡፡

በሕክምና ላይ ችግር የሚፈጠርና የሚያጋጥም ቢሆንም እንደዚህ ያለ ስህተት ግን በተለይ በዘውዲቱ መታሰቢያ ሆስፒታል አጋጥሞ እንደማያውቅ ገልጸው፣ ከመድኃኒት ጋር በተያያዘ ግን የሚፈጠሩ ችግሮች ቢኖሩም ሳይታወቅ ተሸፋፍነው እንደሚያልፉ ተናግረዋል፡፡ በሰላም ደሞዜ ላይ የተፈጸመው ስህተት ግን በመሸፋፈን የሚታለፍ ባለመሆኑ ሊታወቅ መቻሉን አክለዋል፡፡

የአንገቷን እንቅርት በቀዶ ጥገና ለማስወገድ ሄዳ ጤነኛ ሆዷም ተቀዶ በሆስፒታሉ አንደኛ ፎቅ ላይ ተኝታ የምትገኘውን ሰላም ደሞዜን ሪፖርተር አነጋግሯታል፡፡

ለቤተሰቦቿ ሁለተኛ ልጅ የሆነችውና በኦሮሚያ ክልል አርሲ ዞን አስኮ ቀበሌ ውስጥ ተወልዳ እስከ 13 ዓመቷ ድረስ እዚያው ማደጓን የምትናገረው ሰላም ደሞዜ፣ ላለፉት አሥር ዓመታት ወደ አዲስ አበባ መጥታ ከእህቷ ጋር እንደምትኖር ትናገራለች፡፡

የ23 ዓመቷ ወጣት የግል ሥራ እየሠራች ከእህቷ ጋር ስትኖር አንገቷ ላይ ያበጠውን እንቅርት ለማስወገድ የያዘችው ወረፋ ለሆዷም መትረፉ እንዳሳዘናት ገልጻለች፡፡ እንደ ሕመም ቆጥራው በቀዶ ሕክምና እንደሚድንላት ሙሉ እምነት ይዛ ወደ ሆስፒታሉ በመሄዷ በአንገቷ ላይ የተደረገው ቀዶ ጥገና ምንም እንደማይሰማት ተናግራለች፡፡

ነገር ግን እሷም ሳታስበውና በማታውቀው ሁኔታ ተከፍቶ የተዘጋው ጤነኛ ሆዷ ግን ጥዝጣዜው አላስተኛ እንዳላት ትናገራለች፡፡

ዶክተሮቹ አይተዋት፣ ‹‹ቅዳሜ ሚያዝያ 15 ቀን 2008 ዓ.ም. ትወጫለሽ ብለውኛል፤›› ካለች በኋላ ፊቷ ክፍት ብሎትና የግንባሯ ቆዳ ተሸብሽቦ ሕመሟን ማዳመጥ ቀጥላለች፡፡

ለሐሞት ጠጠር ቀዶ ጥገና ወደ ሆስፒታሉ የሄደችው ሰላም ኪሮስ ማደንዘዣ ወስዳ የነበረች ቢሆንም፣ በስህተት አንገቷ በቀዶ ጥገና ሊከፈት ሲል ራሷን ተከላክላ ማዳኗ ታውቋል፡፡ ስህተት በመሥራታቸው የተደናገጡት የሕክምና ባለሙያዎቹ በኋላ ግን የሐሞት ጠጠር ቀዶ ጥገና አድርገውላት በመልካም ጤንነት ላይ እንደምትገኝ መረዳት ተችሏል፡፡ Source :Reporter