Widgetized Section

Go to Admin » Appearance » Widgets » and move Gabfire Widget: Social into that MastheadOverlay zone

‹‹ስለመንግሥት ኃያልነት ወይም ስለሙስና እየተጨነቃችሁ የልማታዊ መንግሥት መርሆዎችን ባታጠፉ መልካም ነው››

kiesen in japan
ፕሮፌሰር ጎ ሺማዳ፣ የጃፓን የኢኮኖሚክስ ምሁር

ዶ/ር ፕሮፌሰር ጎ ሺማዳ ከጃፓን ምሁራን መካከል ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት በርካታ ሥራ ከሠሩ መካከል ናቸው፡፡ ፕሮፌሰሩ ካይዘን የተባለውንና በጥራትና በምርታማነት ላይ ያነጣጠረ የጃፓኖች የማኔጀመንት ፍልስፍናን ለኢትዮጵያ በማስተዋወቅ ረገድ ከሚጠቀሱት መካከል ይመደባሉ፡፡ ‹‹ካይዘንን እኛ አልፈጠርነውም ከአሜሪካ ተዋስነው እንጂ›› የሚሉት ፕፎፌሰር ሺማዳ፣ ‹‹ይልቁንም የራሳችን እስኪመስል ድረስ፣ እኛው የፈጠርነው እስኪመስል ድረስ ባህላችን አድርገነዋል፤›› ይላሉ፡፡ ይህንን ፍልስፍና ለቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በማካፈል ፍላጎት እንዲያድርባቸውና በኢትዮጵያም መተግበር እንዲጀምር የመጀመሪያውን ዕርምጃ የተራመዱት ፕሮፌሰር ሺማዳ፣ ስለጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚገልጹት አላቸው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የልማታዊ መንግሥት ርዕዮተ ዓለም አቀንቃኝ እንደነበሩ ይታወቃል፡፡ ብቻቸውን ግን አልነበሩም፡፡ አብረዋቸው ከነበሩ መካከል እኚሁ ፕሮፌሰር ሺማዳ አንዱ ናቸው፡፡ ነገር ግን ጠቅላይ ሚኒስትሩና ፕሮፌሰር ሺማዳ ሌላም ሦስተኛ ሰው አብሯቸው የልማታዊ መንግሥት ጎዳና ጠራጊ በመሆን መሳተፉን አስፍረዋል፡፡ የአቶ መለስ የቅርብ ወዳጅ መሆናቸው የሚነገርላቸው ዕውቁ የኢኮኖሚክስ ምሁር ጆሴፍ ስቲግሊትዝም አሉበት፡፡ ሦስቱ ሰዎች በሦስት ነገሮች ላይ አንድ ዓይነት ነበሩ፡፡ በካይዘን ፍልስፍና፣ በልማታዊ መንግሥት አስተምህሮና በአፍሪካዊ የገንዘብ ተቋማት ምሥረታ ላይ፡፡ ሦስቱም አፍሪካ ተኮር የልማት መንግሥት መስፋፋት ላይ፣ አፍሪካ ተኮር የፋይናንስ ተቋማት መቋቋም ላይ፣ እንዲሁም አፍሪካ ተኮር የኢኮኖሚ ትራንስፎርሜሽን መርሆዎች ላይ የጋራ መግባቢያ እንደነበራቸው ፕሮፌሰር ሺማዳ በቅርቡ አዲስ አበባ ለስብሰባ በመጡበት ወቅት ከሪፖርተር ጋር በነበራቸው ቆይታ አብራርተዋል፡፡ ብርሃኑ ፈቃደ በእነዚሁ ነጥቦች ላይ በማጠንጠን ከፕሮፌሰር ሺማዳ ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡

ሪፖርተር፡- የጃፓን መንግሥት የካይዘን ሥርዓት በአፍሪካ እንዲተገበር እየጣረ ይገኛል፡፡ ነገር ግን በአፍሪካ ካለው ዝቅተኛ የማኑፋክቸሪንግ ደረጃና ዝቅተኛ ከሆነው የኢንዱስትሪው ዘርፍ አኳያ፣ ከሌሎች ቀጣናዎች አንፃር ሲታይ አፍሪካ ካይዘንን እንዴት እየተገበረች ነው? ለካይዘን ምቹ አኅጉር ናት ማለት ይቻላል?

ፕሮፌሰር ሺማዳ፡- ካይዘን ከመነሻው የጃፓን ቢመስልም ነገር ግን ዓለም አቀፋዊ ነው፡፡ ማንኛው ነው የተሻለ የሥራ ቦታ እንዲኖረው ይፈልጋል፡፡ የትኛውም ሰው ከአለቆቹ ጋር ጥሩ የሥራ ግንኙነት እንዲኖረው ይፈልጋል፡፡ ካይዘን እንደ ዓለም አቀፍ ሥርዓትነቱ በየትኛውም የሥራ መስክና በየትኛውም ቦታ መተግበር ይችላል፡፡ ለምሳሌ ያህል በጋዜጣ አሳታሚ ድርጅት ውስጥ፣ በሆቴል፣ በሆስፒታልና በሌሎችም የሥራ መስኮች መተግበር ይችላል፡፡ መሠረታዊው ትኩረቱ ጥራትን ማስጠበቅ ነው፡፡ የጃፓን ኢኮኖሚ ማደግ የቻለው በካይዘን አማካይነት ነው፡፡ ቶዮታ ቀድሞ ተነሳሽነቱን ወስዶ ነበር፡፡ የኩባንያው ፍልስፍና በካይዘን ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ቀደም ብሎም ሆነ ካከተመም በኋላ ትንሽ ኩባንያ የነበረው ቶዮታ፣ በአሁኑ ወቅት በዓለም የመኪና ኢንዱስትሪ ውስጥ ጉልህ ተፅዕኖ ፈጣሪ ሆኗል፡፡ የካይዘንን ታሪክ ወደ ኋላ ካየን ከቶዮታ ጋር የሚያያዝ ነው፡፡ ለማለት የምፈልገው ነገር ምንድን ነው? በአፍሪካ ትልቅ አምራች ኩባንያዎች ባይኖሩና ትልቅ የኢንዱስትሪ መስክ ባይፈጠርም ካይዘንን ግን መተግበር ይቻላል ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ጃፓን ከገነባችው ጠንካራ ኢኮኖሚ አኳያ ሲታይ በአፍሪካ በተለይም በኢትዮጵያ ያለው የካይዘን ትግበራ እንዴት ይታያል?

ፕሮፌሰር ሺማዳ፡- የጃፓን ኩባንያዎችን ከአፍሪካ ጋር ማወዳደር ይከብዳል፡፡ ሲጀመር በሁለቴ መካከል ታሪካዊ ልዩነት አለ፡፡ ሆኖም በአፍሪካ ያለውን ከሌሎች አኅጉሮች አኳያ ካየነው በአፍሪካ የሚያስገርም ነገር እንዳለ መናገር እችላለሁ፡፡ የጃፓን ዓለም አቀፍ የትብብር ኤጀንሲ (ጃይካ) በዓለም ዙሪያ የካይዘን ፕሮጀክቶችን ይተገብራል፡፡ እናም ከሌላው ይልቅ አፍሪካ በተሻለ ደረጃ ከካይዘን ጋር ቁርኝት አላት፡፡ በተለይ ኢትዮጵያ በአስገራሚ ሁኔታ ከሌሎች በተሻለ ካይዘንን ተቀብላ በመትግበር ላይ ነች፡፡ የከፍተኛ ኃላፊዎች ቁርጠኝነት አለ፡፡ የኢትዮጵያ ካይዘን ኢንስቲትዩት ተነሳሽነት የትም ቦታ የማይታይ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ካይዘንን በትኩረት ስለምትመለከተው በአገሪቱ ብሔራዊ ንቅናቄ እስከመሆን ደርሷል፡፡ ይህ ዓይነቱ ነገር በጣም ወሳኝ ግብዓት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በዚህ አገር ለመሻሻልና ለመለወጥ የመጣጣርና የመፈለግ ነገር ይታያል፡፡ ይህ እንዳለ ሆኖ ግን ሌሎች የማኔጅመንት ፍልስፍናዎች እየተተገበሩ ባለበት ጊዜ፣ ጃፓን ካይዘንን ወደ አፍሪካ በማምጣት እንዲተገበር የምትፈልግበት ምክንያት ምንድነው?

ፕሮፌሰር ሺማዳ፡- ነገሩ ከእኛ የተሞክሮ ታሪክ ጋር የሚያያዝ ነው፡፡ አዎ መሠረታዊ የሥራ ሒደት የሚባለውን እናውቃለን፡፡ ሌሎችም ሥርዓቶችንም እናውቃለን፡፡ ነገር ግን ሁሉንም የምናውቃቸው ከመጻሕፍት እንጂ ከልባችን አይደለም፡፡ ካይዘንን ከአንደኛ ደረጃ ትምህርታችን ጀምሮ ከልብ እናውቀዋለን፡፡ ስለካይዘን እየተማርን ነው ያደግነው፡፡ በሕይወታችንም ሆነ በኩባንያዎቻችን ብቃት ላይ መሻሻል እንድናሳይ ያግዘናል፡፡ ነገሮችን እንዴት ማከናወን እንደሚቻል የምናውቅበትና ከልባችን የምናደርገው ነገር ነው፡፡ ካይዘንን በአፍሪካ ለማስተዋወቅ ይህ አንደኛው ዋና ምክንያት ነው፡፡ በቀደሙት ጊዜያት ሆንዳና ቶዮታ በጣም አነስተኛ ኩባንያዎች ነበሩ፡፡ ከጋራዥነት ነው የጀመሩት፡፡ በአሁኑ ጊዜ ግን በዓለም ላይ ትልቅ ቦታ የያዙ ግዙፍ ኩባንያዎች ለመሆን በቅተዋል፡፡ በአፍሪካም ይህን ዓይነቱን ስኬት በማምጣት የአፍሪካን ስኬታማ ታሪክ ለተቀረው ዓለም መተረክ እንፈልጋለን፡፡

ሪፖርተር፡- ከጅምሩ ካይዘን በጃፓን መተግበር የጀመረው በግሉ ዘርፍ ፍላጎት ተመርቶ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ግን መንግሥት ተነሳሽነቱን ወስዶ ለማስተግበር እየተንቀሳቀሰ በመሆኑ በዚህ ላይ ምን ይላሉ? በእንዲህ ያለው አካሄድ ኩባንያዎች ልክ እንደ ጃፓኖቹ በስኬት መራመድ ይችላሉ?

ፕሮፌሰር ሺማዳ፡- ልዩነት አይኖረውም፡፡ የጃፓን የግል ዘርፍ ካይዘንን ለመተግበር ተነሳሽነቱን ወስዷል ስንል እንዳንሳሳት፡፡ እንዲዚያ አይደለም፡፡ በቀደሙት ዓመታት የጃፓን መንግሥት ነው ተነሳሽነቱን በመውሰድ ካይዘንን ለመተግበር የተነሳው፡፡ ከአሜሪካ ዕርዳታ አግኘተን ነበር፡፡ ልክ እንደ ኢትዮጵያ ካይዘን ኢንስቲትዩት ያለውንና የጃፓን የምርታማነት ማዕከል የሚባል ተቋም መሥርተናል፡፡ ኢትዮጵያ ከጃፓን ባገኘችው ዕርዳታ ነው የካይዘን ኢንስቲትዩት የተቋቋመው፡፡ ኢንስቲትዩቱ የካይዘን ሥርዓትን ለማስተግበር እየሠራ ያለ ተቋም ነው፡፡ በጃፓን ከመነሻው ካይዘን በመንግሥት ተነሳሽነት ነበር መተግበር የጀመረው፡፡ እንደየአገሮቹ ሁኔታ የካይዘን ዕውቀትን የማዳረሱ ሥራ እኩል አልሄደም፡፡ በአንዳንድ አገሮች የመንግሥት ተቋማት ደህና ሲንቀሳቀሱ በሌሎች አገሮች ደግሞ የግሉ ዘርፍ ካይዘንን በመተግበር የተሻለ ሆኖ ይገኛል፡፡ ከመጀመሪያው ሲታይ በጃፓን ካይዘንን በማስተዋወቁ ተግባር ላይ የመንግሥት ተቋማት ጥሩ ሥራ ሠርተዋል፡፡ ከዚያ በኋላ ግን የጃፓን ኩባንያዎች ካይዘንን በመተግበር ረገድ ጠንካራ ነበሩ፡፡ ዕውቀቱ ውጤታማ ነበር፡፡ በደቡብ ኮሪያ መንግሥት ነበር በአተገባበሩ ላይ ውጤታማ ሥራ የሠራው፡፡ ስለዚህ ዋናው ጉዳይ ያለው ከሚያስተዋውቀው ወይም ከሚተገብረው አካይ ሳይሆን ከሥርዓቱ ይዘት ላይ ነው፡፡ የኢትዮጵያን ካየን የመንግሥት ተቋማት ናቸው ደህና እየሠሩ ያሉት፡፡ የሚታየው ነገር በጣም ጥሩ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የአፍሪካ አገሮች ካይዘንን ከልባቸው መተግበር ጀምረዋል ብለው ያምናሉ? ምንስ ቢያደርጉ ነው ጃፓን የደረሰችበት ደረጃ ላይ የሚደርሱት?

ፕሮፌሰር ሺማዳ፡- እውነት ለመናገር ይህንን አላውቅም፡፡ ወደ ኢትዮጵያ ከመጣሁ አምስት ዓመት አልፎኛል፡፡ በእነዚህ ዓመታት ውስጥ ሲካሄዱ የነበሩትን ነገሮች መረዳት ይኖርብኛል፡፡ እንደተነገረኝ ከሆነ ግን ኢትዮጵያውያን ካይዘንን ከልብ ወደውታል፡፡ አንዳንድ ሰዎች ካይዘንን በሚገባ ተረድተው በራሳቸው መንገድ ሲገልጹት አይቻለሁ፡፡ ለምሳሌ የኢትዮጵያ ካይዘን ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ከካይዘን ጋር ያላቸውን ዝምድና ማየት እችላለሁ፡፡ እሳቸው ስለካይዘን ሲገልጹ በካይዘን ሥርዓት ያደገ ሰው እንዴት ሰዎች ከልባቸው እየተቀበሉት እንዳሉ መገመት አያዳግተውም፡፡ ሌሎች በርካታ ሰዎችም በአጭር ጊዜ ውስጥ ከካይዘን ጋር የሚኖራቸው ቅርርብ በጣም የጠበቀና ከልብ እንደሚሆን አምናለሁ፡፡ ካይዘንን ከአሜሪካኖች እንደተማርነው ማስተዋል አለብህ፡፡ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ 4,000 ጃፓናውያንን ወደ አሜሪካ በመላክ ስለካይዘን ዕውቀት እንዲጨብጡ አድርገናል፡፡ ከአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ኤጀንሲ (ዩኤስኤኣይዲ) ካይዘንን ለመማር የሚያስችሉ ዕርዳታዎችን አግኘተን ነበር፡፡ ዛሬ ግን የትኛውንም ጃፓናዊ የካይዘን ዕውቀት ከየት እንደመጣ ብትጠይቀው ትክክለኛውን ምላሽ ላይሰጥህ ይችላል፡፡ ምክንያቱም ካይዘን ባህላችን ሆኖ ከደማችን የተዋሀደ በመሆኑ፣ ካይዘንን ከውጭ ያመጣነው ነው ብሎ ለማመን ስለሚያዳግት ነው፡፡ አንዳንድ ሰዎች የጃፓን ሥርዓት የሆነውን ካይዘን በአፍሪካ መተግበር እንዴት እንደሚቻል በማሰብ ይጠይቁኛል፡፡ ነገር ግን እኛም ከጅምሩ ከአሜሪካኖች የተማርነው መሆኑን አያውቁም፡፡ የሚያስቡት ጃፓን የካይዘን ፍልስፍናን ቀድማ እንዳመነጭች አድርገው ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ካይዘንን በአንዳንድ መስኮች ላይ ማስተዋወቁም ሆነ መተግበሩ ፈተና እንደማያጣው ግልጽ ነው፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች ይህ ሥርዓት እንዲተዋወቅ ሲደረግ ሒደቱና ፈተናው እንዴት ነበር?

ፕሮፌሰር ሺማዳ፡- በኢትዮጵያ አሁን ያን ያህል ፈታኝ ነው ማለት አይቻልም፡፡ ምክንያቱም በርካታ ሰዎች ስለካይዘን ስለሚያውቁ ማለት ነው፡፡ በሌሎች የአፍሪካ አገሮችም ካይዘንን እያፋፋን ነው፡፡ ለጀማሪ አገሮች ካይዘንን ማስተዋወቅና መተግበር ከጀምሩ ምናልባት ፈታኝ ሊሆን ይችላል፡፡ ምናልባትም ካይዘን ስለሚያስገኘው ጠቀሜታ ብዙም ሊረዱ አይችሉም፡፡ ይህ እንደየአገሩ ሁኔታ ይለያያል፡፡

ሪፖርተር፡- ኢትዮጵያ በአፍሪካ የካይዘን ማዕከል በመሆን በመጪዎቹ አሥር ዓመታት ውስጥ የት መድረስ እንደምትፈልግ ዕቅድ አውጥታለች፡፡ ምናልባትም ካይዘንን በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እስከ ዶክትሬት ዲግሪ ለማስተማር በመነሳት ብቸኛዋ አገር ሳትሆን አትቀርም፡፡ ይህ መደረጉ አገሪቱን እንዴት ሊጠቅማት እንደሚችል ቢያብራሩልን? ይህንን ማድረጉ የተለመደና የሚመከር ነው ብለው ያስባሉ?

ፕሮፌሰር ሺማዳ፡- አዎን፡፡ በካይዘን መስክ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሥልጠና መኖሩ በጣም ጠቃሚ ነገር ነው፡፡ የትምህርት ሥልጠና መኖሩ መደበኛውን የሥራ ማዕድ ለመቀላቀል ይጠቅማል፡፡ ብዙ በመማር ሥራ ለማግኘት የሚረዳንን የምስክር ወረቀት ለማግኘት እንጥራለን፡፡ በመሆኑም በቅድመ ምረቃ፣ በድኅረ ምረቃ፣ እንዲሁም በዶክትሬት ደረጃ ሥልጠና የሚሰጥባቸውን ፕሮግራሞች መጀመር የሚበረታታ ተግባር ነው፡፡ ይህ ሲደረግ ወጣቱ ትውልድ ስለካይዘን ይበልጥ እንዲያውቅ የሚያበረታታው ነገር ነው፡፡ ነገር ግን ፈተናውንም ማሰብ ያስፈልጋል፡፡ ለአዲስ ተመራቂዎች የሥራ ዕድል ስለምትፈጥርበት መንገድ ማሰብ መቻል አለብህ፡፡ እንደ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር የተመራቂዎች ሥራ ማግኘት መቻል አለመቻላቸው በጣም ያሳስበኛል፡፡ እንደማስበው የትኛውም ዩኒቨርሲቲ ይህንን መገንዘብ ይኖርበታል፡፡ በካይዘን አማካይነት የሚሰጡ ትምህርቶች ተመራቂዎች ቁጥርና ከእነሱ ብዛት ጋር የሚዛመድ የሥራ ዕድል ስለመኖሩ ማሰብ ያስፈልጋል፡፡

ሪፖርተር፡- ከታዋቂው የኢኮኖሚ ባለሙያ ጆሴፍ ስቲግሊትዝ ጋር ስላላችሁ ቀረቤታ እንነጋገር፡፡ አብራችሁ መጻሕፍት ጽፋችኋል፡፡ አብራችሁ መሥራት እንዴት እንደጀመራችሁ ሊገልጹልን ይችላሉ?

ፕሮፌሰር ሺማዳ፡- እ.ኤ.አ. በ2005 በኒውዮርክ ለሚገኘው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጃፓን ኤምባሲ ሠራተኛ ሆኜ እሠራ ነበር፡፡ በዚህ ጊዜ ነበር ከጆሴፍ ስቲግሊትዝ ጋር አብሮ የመሥራት ዕድል የተፈጠረው፡፡ በወቅቱ የሚሊኒየሙ የልማት ግቦችን በሚመለከት የጃፓን ሚና ላይ አብሮ ለመሥራት የሚያስችል ትብብር ለመፍጠር ፈለግን፡፡ ጃፓን የሚሊኒየሙ የልማት ግቦች ውጤታማ አተገባበር እንዳይኖራቸው የሚያደርጉ ፈተናዎችን በመጋፈጥና ውጤታማ በመሆን፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚተገበሩት መንገድ ላይ እየሠራን ነበር፡፡ በወቅቱ ጆሴፍ ስቲግሊትዝን ይበልጥ እንዳውቃቸው የረዳኝ የጃይካ ባልደረባ ሆኜ ለመሥራት ተቋሙን ዳግመኛ ስቀላቀል ነበር፡፡ በጊዜው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽን ኮሚሽነርና የጃይካ ፕሬዚዳንት የነበሩት ሳዳኮ ኦጋታ ጆሴፍ ስቲግሊትዝ በምርምር መስክ ከጃይካ ጋር በትብብር እንዲሠሩ እንዳደርግ ጠይቀውኝ ነበር፡፡ በዚያ መሠረት ነበር ከእሳቸው ጋር አብሮ መሥራት የጀመርነው፡፡ የመጀመሪያው መጽሐፋችን በኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ፕሬስ አማካይነት ታትሟል፡፡ እርግጥ በመጀመሪያው መጽሐፍ ላይ ምንም ነገር ባልጽፍም፣ ‹‹ኢንዱስትሪያል ፖሊሲ ኤንድ ኢኮኖሚክ ትራንስፎርሜሽን ኦፍ አፍሪካ›› በተሰኘው ሁለተኛው መጽሐፋችን ውስጥ ግን በጽሑፍ ተሳትፎ አድርጌያለሁ፡፡ በመጪው ጥቅምት ሦስተኛውን መጽሐፍ እናሳትማለን ብለናል፡፡ አራተኛውንም በጋራ እየጻፍን እንገኛለን፡፡

ሪፖርተር፡- አራተኛው መጽሐፋችሁ ስለምን ይናገር ይሆናል? እሱም ስለአፍሪካ የሚናገር ይሆን?

ፕሮፌሰር ሺማዳ፡- እርግጥ ስለአፍሪካ ብቻ አይደለም፡፡ በርካታ ሰዎች በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ይገረማሉ፡፡ ምንም እንኳ መጽሐፉ ስለአቶ መለስ ባያወራም ነገር ግን እሳቸው አፍሪካ የራሷ የልማት ባንክ ሊኖራት ይገባል በማለታቸው ይታወሳሉ፡፡ ስለዚህም መጽሐፉ አፍሪካዊ የሆነ የልማት ባንክ መመሥረት አስፈላጊነት ላይ ያተኮረ ነው ማለት ነው፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ሐሳብ መነሻ ሆኖናል፡፡

ሪፖርተር፡- ጠቅላይ ሚኒስትር መለስና ስቲግሊዝ የቅርብ ወዳጆች ነበሩ፡፡ አንዳንዶች በኢኮኖሚክስ ጽንሰ ሐሳቦች ላይ መለስን አስተምረዋል ሲሉ ስለስቲግሊትዝና ስለአቶ መለስ ቅርበት ሲናገሩ ይደመጣሉ፡፡ ሦስታችሁ እንዴት እንደተገናኛችሁ ቢነግሩን?

ፕሮፌሰር ሺማዳ፡- ሁለቱ የቅርብ ወዳጆች ነበሩ፡፡ ይህንን በደንብ አውቅ ነበር፡፡ በዚህም ሰበብ ነው የካይዘን ጽንሰ ሐሳብን ለአቶ መለስ ያስተዋወቅናቸው፡፡ ስቲግሊትዝን ወደ አዲስ አበባ አምጥተናቸው ነበር፡፡ በአቶ መለስ፣ በስቲግሊትዝና በጃይካ ኃላፊዎች መካከል ስብሰባ እንዲዘጋጅ አደረግን፡፡ ስለካይዘን ባስረዳናቸው ጊዜ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ፍላጎቱ አደረባቸውና ሐሳቡን ይበልጥ ለማዳበር ፈለጉ፡፡ በኋላም ካይዘን በኢትዮጵያ ውስጥ መተግበር ስለሚችልበት መንገድ መላ እንድንፈልግ ጠየቁን፡፡

ሪፖርተር፡- ስለዚህ እርስዎም ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ካይዘንን ለኢትዮጵያ እንዲያስተዋውቁ ካግባቡት መካከል አንዱ ነበሩ ማለት ነው?

ፕሮፌሰር ሺማዳ፡- እኔ እንጃ? ማለት ትችላለህ፡፡

ሪፖርተር፡- የአፍሪካ የኢኮኖሚ ትራንስፎርሜሽን የወቅቱ መነጋገሪያ ርዕሰ ጉዳይ ይመስላል፡፡ ነገር ግን በአፍሪካ የማኑፋክቸሪንግ መሠረት ባለመኖሩና የኢንዱስትሪ መዋቅርም ባለመዘርጋቱ አፍሪካውያን ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ለመለወጥ ዝግጁ ናቸው ወይ የሚል ጥያቄ ያስነሳል፡፡ በመሆኑም ስለትራንስፎርሜሽን ለማውራት እርግጥ ጊዜው አሁን ነው? ስለዚህ ምን የሚሉት ነገር አለ?

ፕሮፌሰር ሺማዳ፡- ትራንስፎርሜሽን ማለት ወዲያውኑ የሚመጣ ለውጥ ማለት እንዳልሆነ ማስተዋል አለብን፡፡ እ.ኤ.አ. ከ1990ዎቹ ጀምሮ እርግጥ የአፍሪካ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ቀስ በቀስ እያሽቆለቆለ መጥቷል፡፡ ስለዚህ አንድ ነገር ማድረግ መጀመር አለብን፡፡ የሚያሽቆለቁለውንም የማኑፋክቸሪንግ መስክ በመቀልበስ እንዲያድግ ማድረግ መቻል አለብን፡፡ ይህ ደግሞ ስለትራንስፎርሜሽን እንድንነጋገር ይጋብዘናል፡፡ ይህንን መናገር ይኖርብኝ እንደሆነ ባላውቅም ትልቁ ልዩነት ያለው በመንግሥት ሚናና በልማታዊነት አካሄድ ላይ ነው፡፡ አፍሪካ በመዋቅራዊ ለውጥ ፕሮግራም ምክንያት ብዙ እንደተጎዳች ግልጽ ነው፡፡ በዚህ ፕሮግራም አማካይነት በዓለም አቀፍ ተቋማት ለአኅጉሪቱ የታዘዙላት የፖሊሲ ማዕቀፎች ለአፍሪካ ልማት ያበረከቱት አስተዋጽኦ ኢምንት ነው፡፡ በዚህ ሳቢያ ጆሴፍ ስቲግሊትዝ በጠቅላይ ሚኒስትሩ አስተሳሰቦች ሊማረኩ ችለዋል፡፡ የአቶ መለስ የልማታዊ መንግሥት አስተሳሰብ ለስቲግሊትዝ መነሻ ሐሳብ የሚሰጡ ይዘቶች ነበሩት፡፡ ከዚህ በኋላ ነበር ስቲግሊትዝ የብራዚል፣ የህንድ፣ የሩሲያ፣ የቻይናና የደቡብ አፍሪካ ጥምረት የሆነውና ‹‹ብሪክስ›› የተሰኘው ቡድን የራሱን ባንክ እንዲያቋቁም ማስተጋባት የጀመሩት፡፡ ከዚህም ባሻገር የእስያ መሠረተ ልማትና ኢንቨስትመንት ባንክ እንዲቋቋምም ስቲግሊትዝ ድጋፋቸውን ሰጥተዋል፡፡ ስቲግሊትዝ የልማታዊ መንግሥት ርዕየተ ዓለምን በማቀንቀን የኢንዱስትሪ ፖሊሲና ካይዘንንም ለአፍሪካ አገሮች የትራንስፎርሜሽን መሣሪያዎች አድርገው የሚመለከቱ ምሁር ናቸው፡፡ ነገሮችን በአንድ ሌሊት ልትቀይራቸው አትችልም፡፡ አገሮች የኢኮኖሚ አውታሮቻቸውን ያዋቀሩባቸውን መንገዶች በአንድ ጊዜ ልትለውጥ አትችልም፡፡ ነገር ግን መንግሥታት ወደ ትራንስፎርሜሽን የሚወስዳቸውን መንገድ እንዲቀይሱ ማድረግ ግን ይቻላል፡፡ ወደዚያ የሚያደርሳቸውን መንገድ ማስተካከል ይችላሉ፡፡

ሪፖርተር፡- ስቲግሊትዝ፣ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትርና እርስዎ የልማታዊ መንግሥት መርህን በመደገፍ ተመሳሳይ አቋም ትጋራላችሁ፡፡ ሆኖም ልማታዊ መንግሥት የሚባለው ጽንሰ ሐሳብ መንግሥታት ይበልጥ ተፅዕኖ መፍጠር የሚችሉበትን ዕድል የሚሰጥ ርዕዮተ ዓለም ነው በማለት የሚኮንኑት አሉ፡፡ ይህንን ጽንሰ ሐሳብ የማይደግፉ ሰዎች ከፖለቲካዊ ጫናው ወይም የመናገር ነፃነትንና ሌሎችንም ከመገደቡ ባለፈ የግሉ ኢኮኖሚ በመንግሥት ተፅዕኖ ሥር እንዲሆን የሚያስገድድ ርዕየተ ዓለም ነው ብለው ይከራከራሉ፡፡ እነዚህን መከራከሪያዎች እንዴት ይመለከቷቸዋል?

ፕሮፌሰር ሺማዳ፡- አፍሪካ የመዋቅራዊ ለውጥ ፕሮግራሞች ተብለው በተጻፉላት ፖሊሲዎች ሳቢያ ብዙ መጎዳቷን መርሳት የለብንም፡፡ የመዋቅራዊ ለውጥ ፕሮግራሞች ዋና ዓላማ ገበያ መር አካሄድን የሚያቀነቅኑ በመሆናቸው በኢኮኖሚው ውስጥ የተፈጠሩ ችግሮችን ሁሉ ገበያው ብቻ እንዲፈታቸው ይፈልጋሉ፡፡ ይህ ቀኖናዊ መርህ ነው አፍሪካ ላይ ተጭኖ የነበረው፡፡ እንዲህ ያለው ፖሊሲ በብዙ ፈርጁ አፍሪካ ላይ ችግር አምጥቶ ነበር፡፡ ነገር ግን የትኛውንም የእስያ አገር ስትመለከት አብዛኞቹ አገሮች ለኢንዱስትሪያቸው መጎልበት የልማታዊ አስተሳሰብ አስተዋጽኦ ማድረጉን ይገልጹልሃል፡፡ ቻይና፣ ደቡብ ኮሪያ፣ ጃፓን፣ ኢንዶኔዢያ፣ ታይላድና ሌሎችም አገሮች የልማታዊነት መንግሥት መንገድ የተከተሉ ናቸው፡፡ አፍሪካውያን ግን ከዚህ ውጪ ለመሆን ተገደው ነበር፡፡ ስለዚህ አሁን ያለው ልማታዊ አካሄድ ቀድሞ ከመነሻው ወደነበረበት የመመለስ ጉዞ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት በርካታ የአፍሪካ አገሮች ልማታዊ መንግሥት ለመሆን ፍላጎት አላቸው፡፡ በንድፈ ሐሳብ ደረጃ፣ ስቲግሊዝ ገበያው የሁላችንንም መሠረታዊ ጥያቄዎች የመመለስ አቅም የለውም ብለው ይከራከራሉ፡፡ ገበያው የሆነ ቦታ ላይ ምላሽ ሊሰጠን አልቻለም፡፡ የምትፈልገውን ምርት ማን እንደሚያመርትልህ ማወቅ በጣም ከባድ ነው፡፡ ገበያው እንዲህ ያለውን ጥያቄ ለመመለስ የሚያስችል አካሄድ የለውም፡፡ ገበያው ለጥያቄህ ምላሽ መስጠት ሲያቅተው፣ መንግሥት ጣልቃ በመግባት የማረጋጋት ሚና ሊኖረው ይገባል፡፡

ሪፖርተር፡- መንግሥት ይህንን የሚያህል ሚና የሚሰጠው ከሆነ በማንኛቸውም የኢኮኖሚና ሌሎች አውታሮች ላይ እጁን የማሳረፍና ጫና የመፍጠር ጉልበት አይኖረውም እንዴ?

ፕሮፌሰር ሺማዳ፡- እርግጥ የተወሰነ ጉዳት ሊኖረው ይችላል፡፡ ሁሉ ነገር ፍጹም አይደለም፡፡ ስለሙስና አብዝታችሁ የምትጨነቁ ከሆነ፣ ወይም መንግሥት በልማታዊ ርዕዮተ ዓለም ምክንያት በጣም ፈርጣማ ክንድ ይኖረዋል ብላችሁ የምትሠጉ ከሆነ፣ ከዚህ ሁሉ ጫና ነፃ መሆን የምትችሉት ቀኖናዊውን የገበያ መር መርህ በመከተል ነው፡፡ ይህም ቢሆን ግን ሊሠራ እንደማችል ሁላችንም የምናውቀው ነው፡፡ ስለዚህ ስለመንግሥት ኃያልነት፣ ስለአስተዳደራዊ ችግሮች ወይም ስለሙስና እየተጨነቃችሁ የልማታዊ መንግሥት መርሆዎችን ባታጠፉ መልካም ነው፡፡ ስለእነዚህ ችግሮች መጨነቅ አይገባም እያልኩ አይደለም፡፡ ስለእነዚህ መጨነቅ አይገባም የሚል አቋም የለኝም፡፡ ነገር ግን ሚዛኑን የማስጠበቅ ሚና ሊኖረን ይገባል፡፡ ጃፓን ከሙስናና ከሌሎችም ችግሮች ነፃ አይደለችም፡፡ ነገር ግን ከእንዲህ ያሉት ስህተቶች እንማራለን፡፡ በመሆኑም ሙስና ስላለ ልማታዊ አስተሳሰብ አያስፈልገንም ልንል አንችልም፡፡ ሙስና ሊኖር ይችላል፡፡ ነገር ግን እንዲህ ካለው መጥፎ ተግባር እንዴት እናገግም የሚለውን ማየት አለብን፡፡ መልካም አስተዳደር እንዴት ይጎለብታል የሚለውን ማየቱ ጠቃሚ ነጥብ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ስለአፍሪካ አመራርና አስተዳደር ሊባል የሚችለው ነገር ምንድነው? አፍሪካ የልማታዊ መንግሥት ንድፈ ሐሳቦችን በሙሉ አቅም ለመተግበር ምን ያህል ብቁ ናት?

ፕሮፌሰር ሺማዳ፡- እኔ የፖለቲካ ሳይንቲስት አይደለሁም፡፡ የአፍሪካ አገሮችን አስተዳደራዊ ጉዳዮችን አውቃለሁ ማለት አልችም፡፡ በጥቅል አነጋገር እየተሻሻለ የመጣ ይመስለኛል፡፡ ይህንን ለማየት አንደኛው መንገድ የኢኮኖሚ ዕድገት ነው፡፡ በመላው አፍሪካ ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገትና ለውጥ በመምጣት ላይ መሆኑን ሁላችንም እያየን ነው፡፡ እ.ኤ.አ. ከ1990ዎቹ አኳያ ሲታይ በአሁኑ ወቅት ግጭቶች እየቀነሱ እንደመጡ መናገር ይቻላል፡፡ ይህ በጥሩ መልኩ እየተለወጠ መምጣቱ እየታየ ነው፡፡ ጥያቄው ግን ይህንን እንዴት ዘላቂ ማድረግ ይቻላል የሚለው ላይ ነው፡፡ ከዚህ የባሰው አደጋ የሚመጣው ደግሞ ከሕዝብ ብዛት አኳያ እየተፈጠረ በመጣው ጫና ምክንያት ነው፡፡ አፍሪካ ከፍተኛ የሕዝብ ዕድገት ቁጥር በማስመዝገብ ላይ ነች፡፡ እያደገ ለመጣው የሕዝብ ቁጥር ሥራ መፍጠር ካልቻሉ፣ ወጣቱ ትውልድ የቀን ተቀን ሕይወቱን ለመምራት የሚያስችለው ነገር ካላገኘ፣ አገሮች ትልቅ አደጋ ውስጥ ይወድቃሉ፡፡ ለዚህም ነው ሁሉንም ነገር ለገበያው በመተው መፍትሔ እንዲያመጣልህ የማትጠብቀው፡፡

ሪፖርተር፡- ከቶኪዮ የአፍሪካ ልማት ዓለም አቀፍ ኮንፈረንስ (ቲካድ) ጋር በተያያዘ ዘንድሮ ለስድስተኛ ጊዜ የሚካሄደውን ጉባዔ ኬንያ ለማስተናገድ በመዘጋጀት ላይ መሆኗ ይታወቃል፡፡ ይህንን ጉባዔ ጃፓን በአገሯ ማካሄድ ስትጀምር የዕርዳታና የወዳጅነት መገለጫ አድርጋ ነበር፡፡ ከጊዜ በኋላ ግን በቻይና፣ በህንድ፣ በአሜሪካና በሌሎችም አገሮች የተጀመሩ ፎረሞች አፍሪካን አጋር በማድረግ ረገድ ከጃፓኑ ቲካድ በላይ እየታወቁ በመጥተዋል፡፡ ከሃያ ዓመት በላይ ቆይታ ያለው ይህ ጉባዔ እንደሚገባው ያልታወቀበት ምክንያት ምንድነው? ከኬንያው ስብሰባስ ምን ይጠበቃል?

ፕሮፌሰር ሺማዳ፡- ውድድሩ ከበድ እያለ መጥቷል፡፡ ነገር ግን እነዚህ አገሮች ጃፓን ስለአፍሪካ ልማት ጉባዔ ማዘጋጀት በጀመረችበት ወቅት እነሱም ያዘጋጁ ነበር ወይ ብለን ብንጠይቅ መልሱ አይደለም ነው፡፡ ጃፓን የቲካድ ጉባዔን ማዘጋጀት በጀመረችበት ወቅት ዓለም ፊቱን ከአፍሪካ አዙሮ ነበር፡፡ የምዕራቡ ዓለም ለጋሾች ኦፊሴሊያዊ የልማት ዕርዳታ ለአፍሪካ መስጠት አቁመው ነበር፡፡ የዚህ ዕርምጃ ይበልጥ መገለጫው ደግሞ ለጋሾች ለአፍሪካ መሰጠት ያለበትን የዕለት ደራሽ ዕርዳታ ወደ ምሥራቅ አውሮፓ ማዞራቸው ነው፡፡ በዚህ ጊዜ ነው ጃፓን ወደ አፍሪካ በመምጣት ማገዝ የጀመረችውና ቲካድን ያስተዋወቀችው፡፡ ከዚያ በኋላ ግን የአፍሪካ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት እንደገና ይስባቸው ጀመር፡፡ አንዳንዶቹ የቲካድን ፎርማት እየኮረጁ ነው፡፡ እርግጥ ይህ ጃፓንን ሊጎዳ ቢችልም ለአፍሪካ ግን ጠቃሚ ነው፡፡ በርካታ ሐሳብ የመለዋወጫ መንገዶችና የመወያያ መድረኮች ሲኖሩ ለአፍሪካ መልካም ነገር ነው፡፡ ነገር ግን ቲካድ ብዙም ታዋቂነት ሳያገኝ ከቀረ ለጃፓን ከባድ ይሆንባታል፡፡ ብዙ ማስተዋወቅ ይኖርብናል፡፡Source :Reporter